ህዝቡ በአቶ መለስ ዜናዊ የተንዛዛ የለቅሶ ስርአት ተቃውሞውን እየገለጠ ነው::

ነሀሴ ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የኢሳት ዘጋቢዎች ያነጋገሩዋቸው የህብረተስብ ክፍሎች እንደገለጡት የአቶ መለስ ዜናዊ የተንዛዛ የለቅሶ ስርአት በህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያመጣ ነው።

አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ በኢግዚቢሽን ማእከል ውስጥ በሚካሄደው ባዛር  ባለፈው ሳምንት በ20 ሺ ብር የንግድ ቦታ የገዛ ሰው ለኢሳት እንደተናገረው ፣ የአቶ መለስ ዜናዊን እረፍት ተከትሎ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሆነ የራዲዮ ጣቢያዎች ማስታወቂያዎችን ማስተላለፍ በማቆማቸው፣ የእርሳቸውና በውስጡ ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ ቦታ የገዙ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርገዋል።

የህዝቡን ሀዘን የሚያደናቅፍ ምንም አይነት ስራ መስራት አይቻልም የሚለው የመንግስት መመሪያ ፣ ከውጭ አገር አላቂ እና ፍጆታ እቃዎችን ያመጡ አስመጪዎችንም ክፉኛ መጉዳቱን ነው ነጋዴዎች የሚናገሩት። በፍጥነት ተሽጠው ከባንክ የተበደሩትን ገንዘብ መመለስ የነበረባቸው ነጋዴዎች ማስታዎቂያዎችን ለማስተላለፍ ባለመቻላቸው እቃዎቻቸውን ለመሸጥ አለመቻላቸውን በምሬት ገልጠዋል።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ከሀዘን ውጭ የሆኑ ማስታወቂያዎችን ለማቅረብ ባለመቻሉም ድርጅቱ ለኪሳራ መዳረጉን በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ለኢሳት ተናግረዋል። ጋዜጠኞቹ እንዳሉት ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ቁጣቸውን እየገለጡ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በአማራ ክልል አስለቃሾች እና ፉከራና ሽለላ የሚያሰሙ ሰዎች በቀን 500 ብር እየተከፈላቸው የለቅሶ ስርአት እያደረጉ ነው። የኢህአዴግ ካድሬዎችም ህዝቡን ያለቀሰና ያላላቀሰ በማለት እየለዩ እንደሚገኙ ኢሳት ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጠዋል።

ዩኒቨርስቲዎችም በአቶ መለስ ዜናዊ ምክንያት የምረቃ ስነስርአታቸውን አራዝመዋል፡፡ የመቀሌ እና ዩኒቲ ዩኒቨርስቲዎች የምረቃ ስነ ስርዓታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀብር እስኪፈፀም ላልተወሰነ ጊዜ አራዝመውታል::

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide