ኢሳት (ሰኔ 22 ፥ 2008)
ስኳር በማምረት በሃገሪቱ ያለውን የስኳር ዕጥረት ለመቅረፍ ብሎም የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት የተቋቋመው ህብር ስኳር አክሲዮን ማህበር በመንግስት በኩል በተደረገበት ጫና እንዲሁም ግለሰቦች ባሳደሩበት ተፅዕኖ ሁለቱ ስራ አስኪያጆች ሲሰደዱ ድርጅቱ በህወሃት የጦር ጄኔራሎች በሚመራው ሜቴክ እስረኛ መሆኑ ተገለጸ።
የመጀመሪያው ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ ለገሰ ግፊቶች ሲበረቱባቸው ስራቸውን ለቀው ወደ አሜሪካ መመለሳቸውን ተከትሎ በስራ አስኪያጅነት የተሾሙትና አሁን እርሳቸውም በስደት አሜሪካ የሚገኙት አቶ ምናላቸው ስማቸው ፋብሪካን ለመገንባትና መሬት ለማግኘት የደረሰባቸውን ጫና እና ያለፉበትን ውጣ ውረድ ለኢሳት በዝርዝር ተናግረዋል።
በሃገሪቱ ያለውን ህግ መሰረት አድርገው በአክሲዮን ሽያጭ 40 ሚሊዮን ብር ያህል ከሰበሰቡ በኋላ የተሰጣቸውን መሬት ለውጭ ሃገር ባለሃብት በማስተላለፍ ወይንም እርሱ ቀድሞ ተይዟል የሚል ምክንያት በመስጠት የአክሲዮኑን ሽያጭ እንዲስተጓጎል መደረጉን ዘርዝረዋል።
ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው ያቋቋሙት ህብር ስኳር የአክሲዮን ማህበር፣ ለብራዚሊያዊ ባለሃብት ያለምንም ሊዝ ክፍያ በተሰጠው መሬት ላይ በሽርክና ለመስራት መገደዱን በኋላም የተባለውን ገንዘብ ሊያቅርብ ባለመቻሉ ምንጣሮ ከተካሄደ በኋላ ውሉ መፍረሱን ዘርዝረዋል።
ውሉ ከፈረሰ በኋላ በብዙ ውጣ ውረድ ለህብር ስኳር ፋብሪካ ከአማራ ክልል 6ሺህ 180 ሄክታር መሬት ማግኘቱን አመልክተዋል። ለዚህም ለ40 አመት የሊዝ ክፍያ 110 ሚሊዮን ብር መወሰኑን ከዚህ ውስጥ 3.3 ሚሊዮን ብሩን በቅድሚያ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውንና ይህንኑ መፈጸማቸውን አቶ ምናላቸው ስማቸው ለኢሳት ገልጸዋል።
ይህንን መሬት ተረክበው የቅድሚያ ክፍያውን ፈጽመው ለምጣሮ ሲዘጋጁ፣ አክሲዮን ማህበሩ ውስጥ ሰርገው የገቡ ግለሰቦች ማህበሩ እንዲፈርስ ግፊት ማድረጋቸውን አመልክተዋል። በተለይም የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የነበሩና የ 1 ሚሊዮን ብር አክሲዮን የገዙት መኮንን ደምሴ የተባሉ ግለሰብ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በ18 ቅርንጫፎች የሚገኝ የማህበሩን ገንዘብ እንዲታገድ ማድረጋቸውን፣ ይህም በንግድ ሚኒስቴር ስም ቢሆንም በኋላ ከንግስት ሚኒስትሩ ዕውቅና ውጭ መፈጸሙን አስረድተዋል።
የታገደው የማህበሩ አካውንት ቢለቀቅም የግለሰቡ ግፊትና ጫና መቀጠሉን በመጨረሻ የህብር ስኳን ፋብሪካ የቦርድ አባላት ከየቤታቸውና ከመንገድ ተይዘው ማዕከላዊ ምርመራ ውስጥ መታሰራቸውን ከአቶ ምናላቸው ስማቸው ማብራሪያ መረዳት ተችሏል። ሰባት የቦርድ አባላት ታስረው መሬት ሳይኖራችሁ አክሲዮን ሰብስባችኋል ተብለው የተመረመሩ ሲሆን ሲሆን ፍርድ ቤቱ ህጋዊ መሰረት እንዳላቸው ተመልክቶ በዋስትና እንደፈታቸው መረዳት ተችሏል።
የሚደረግባቸውን ግፊትና ጫና መቋቋም ያልቻሉበት የህብር አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ ለገሰ፣ የንብረት ርክክብ በመፈጸም ሃላፊነታቸውን ለቀው ወደ አሜሪካ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ አቶ ምናላቸው እርቸውን ተክተው የስራ አስኪያጅነቱን ቦታ ይዘው መቀጠላቸው ተመልክቷል።
ህብር ስኳን አክሲዮን ማህበር የሰበሰበው ገንዘብ ወደ 70 ሚሊዮን ብር በመድረሱ ለአገዳ ተክል የምንጣሮ ስራ በሚከናወንበት ወቅት በህወሃቱ የጦር ጀኔራል በብ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው ሜቴክ ፋብሪካውን ለመገንባት ጥያቄ ማቅረቡን፣ ክፍያውንም ፋብሪካው ስራ ከጀመረ በኋላ ትከፍላላችሁ የሚል ውል መፈጸሙን የገለጹት አቶ ምናላቸው ስማቸው የፋብሪካውን የተከላ ስራ ሲጠብቁ አቶ ወልደመስቀል ወልደማሪያም የተባሉ የህወሃት አባል ከሜቴክ ጋር ያገናኘኋችሁ እኔ ነኝ በማለት 7.5 ሚሊዮን ብር ኮሚሽን ይከፈለኝ በሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።
ሜቴክ ፋብሪካው እንዲገነባ እኛ ጥያቄ አላቀረብንም ከኮሚሽን ሰራተኛም ጋር ውል የለንም በሚል ክፍያውን እንዳይከፍሉ ሲያሳውቁ ከፍተኛ ጫናና ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው ጫናው ከርሳቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸው ላይ ጭምር ማረፉን አቶ ምናላቸው ስማቸው ገልጸዋል። ሁሉ ነገር ከአቅማቸው በላይ ሲሆን፣ የንብረት ርክክብ ፈጽመው ሂሳብ ካወራረዱ በኋላ ከነቤተሰቦቻቸው ሃገር ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለምልልስ በዝርዝር ተመልክተዋል።
ለሃገራቸው ትልቅ አላማ የሰነቁ ሰዎች የተሰባሰቡበት ህብር ስኳር የአክሲዮን ማህበር በመንግስትና ከመንግስት ጋር ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች ባሳደሩበት ጫና በዚህ መልክ ፈተና ውስጥ መውድቁን በቁጭት ዘርዝረዋል።