የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ በተካሄደ ግጭት ቢያንስ ሶስት ሰዎች ተገደሉ

ኢሳት (ሰኔ 22 ፥ 2008)

በአዲስ አበባ ከተማ ህገወጥ የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ የተካሄደ እርምጃ ግጭትን ቀስቅሶ ሁለት የፖሊስ አባላትንና አንድ የወረዳ ስራ አስፈጻሚ ተገደሉ።

በነዋሪዎች ዘንድ ተቃውሞን በቀሰቀሰው በዚሁ ግጭት መሞታቸው ከተረጋገጠው ፖሊሶችና የስራ ሃላፊ በተጨማሪ ሌሎች ፖሊሶችና የወረዳ አስተዳደሮች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በጸጥታ ሃይሎች ላይ ግድያን የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እያደረገ መሆኑን ረቡዕ ምሽት ገልጿል።

የክፍለ ከተማዋ ነዋሪዎች የከተማው አስተዳደር ህገወጥ ያላቸውን የመኖሪያ ቤቶች ለማፍረስ ያስተላለፈው ውሳኔ እጅጉን ቅሬታ እንደፈጠረባቸውና ያልተጠበቀው ሁከት ረቡዕ ረፋድ ላይ መቀስቀሱን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1997 ዓም በኋላ በክፍለ ከተማዋ ተገንብተዋል ያላቸውን ህገወጥ የመኖሪያ ቤቶች ለማፍረስ ሰሞኑን ቤት የመቁጠር ስራን ሲያከናውን እንደነበር ታውቋል።

የቤት ቆጠራውን ተከትሎ በአካባቢው የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እንዲነሳ መደረጉን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ከከተማ አስተዳደር በቤቶች መፍረስ ዙሪያ በቂ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አስረድተዋል።

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ እማኞች አንድ ፖሊስ አንድ ሴትን መደብደብ በጀመረ ጊዜ ግጭቱ ሲቀሰቅስ መቻሉንና ድርጊቱ በስፍራው ውጥረትን ማንገሱን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ግድያውን ፈጽመዋል የተባሉ አካላትን አድኖ ለመያዝ ጥረት እያደረገ መሆኑን ያስታወቁ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።

ባለፈው ወር በቦሌ ክፍለ ከተማ በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ግጭት በትንሹ 10 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የከተማዋ ስፍራዎች በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል ያላቸውን በርካታ መኖሪያ ቤቶች ለማፍረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን በቅርቡ አስታውቀዋል።