የድምጻዊ ታምራት ደስታ የቀብር ስነስርዓት ተፈጸመ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 11/2010)የድምጻዊ ታምራት ደስታ የቀብር ስነስርዓት ተፈጸመ።

ትላንት በድንገት ህይወቱ ያለፈው ድምጻዊ ታምራት ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሙያ ጓደኞቹና አፍቃሪዎቹ በተገኙበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን የቀብር ስነስርዓቱ መፈጸሙ ታውቋል።

በሌላ በኩል የድምጻዊ ታምራት ደስታ የአሟሟቱ ሁኔታ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል።   ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የተሰጠው መርፌ ድንገተኛ ሞቱን ሳያስከትል እንደማይቀር እየተነገረ ነው።

ትላንት ጠዋት በጉሮሮው ላይ መጠነኛ ህመም ይሰማውና የሌሊት ቱታውን እንደለበሰ መኪናውን አስነስቶ ወደ ክሊኒክ ያመራል።

ቶንሲል እያስቸገረው እንደነበረ በዋዜማው ለጓደኞቹ ነግሮአቸዋል። ከዚያ ውጪ ለክፉ የሚዳርግ የጤና ችግር የለበትም።

ትላንት እንደኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት አምስት ሰዓት ላይ ስላሌ ከተሰኘው ክሊኒሊክ ያመራው ድምጻዊ ታምራት ደስታ መኪናው አቁሞ ወደ ክሊኒኩ እየተራመደ ይገባል።

ከደቂቃዎች በኋላ አምቡላንስ ይጠራል። በእግሩ ተራምዶ የገባው ታምራት በቃሬዛ ተደርጎ በአምቡላስ ወደ ሚኒሊክ ሆፒታል ተወሰደ።

የሚኒሊክ ሆስፒታል ሀኪሞች ሲያገኙት ወጣቱ ድምጻዊ ታምራት ደስታ እስከወዲያኛው አሸልቦ ነበር። አስደንጋጭ ያልተጠበቀ ክስተት።

የሚኒሊክ ሆስፒታል የአስክሬን ምርመራ ወደሚደረግበት የጳውሎስ ሆስፒታል እንዲሄድ ያደርጉታል።

እስከዚህ ሰዓት ድረስ የታምራት ደስታ ቤተሰብ፣ ጓደኞቹ የሚያውቁት ነገር የለም።

ታምራት ደስታ በድንገት ወጥቶ ላይመልስ ይህቺን ምድር ተሰናብቷል።

ዛሬ የቀብር ስነስርዓቱ በብዙ ሺህ ህዝብ በተገኘበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

ወዳጆቹ ቤተሰቦቹ የሙያ አጋሮቹና አድናቂዎቹ በከፍተኛ የሀዘን ስሜት ታጅበው ሸኝተውታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስሩ ወርቅነህ ገበየሁና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለአቀባይ መለስ ዓለምም በቀብር ስነስርዓቱ ላይ መገኘታቸው ታውቋል።

በሰሜን አሜሪካ የሙዚቃ ኮንሰርቱን እያቀረበ ያለው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁንም በቀብር ስነስርዓቱ ላይ ተገኝቷል።

ድምጻዊ ታምራት ደስታ በ39ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየበት ክስተት አነጋጋሪ ሆኗል።

ጓደኞቹና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንደሚገልጹት ጊዜ ያለፈበት የተበላሸ መርፌ መወጋቱ ለድንገተኛ ህለፈት ዳርጎታል።

ፖሊስ ምርመራ በማድረግ ላይ ሲሆን የሆስፒታል ምንጮች የህልፈቱን መንስዔ ከተወጋበት መርፌ ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ድምጻዊ ታምራት ደስታ 4 ሙሉ አልበሞችንንና 8 ነጠላ ዜማዎችን በመስራት ተወዳጅነትን ያተረፈ እንደሆነ ከህይወት ታሪኩ ለመረዳት ተችሏል።

ድምጻዊ ታምራት ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበረ።