የአሃዱ ሬዲዮ ባልደረባ ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ተፈታ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 18/2011)በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ለእስር የተዳረገው የአሀዱ ሬዲዮ ባልደረባ ጋዜጠኛ ታምራት አበራ በዛሬው ዕለት ተለቀቀ።

ባለፈው ዓርብ ከሚሰራበት ቦታ ተይዞ ወደ ሰንዳፋ ተወስዶ  የታሰረው  ጋዜጠኛ ታምራት በዋስ መለቀቁን የአሀዱ ሬዲዮ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሊዲያ አበበ ለኢሳት ገልጻለች።

እሷን ጨምሮ ሌሎች የጣቢያው ባልደረቦችም የፊታችን ረቡዕ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የቃል መጥሪያ እንደደረሳቸውም ያገነኘው መረጃ ያመለክታል።

ከአንድ ወር በፊት በተሰራ ዘገባ የተናገርኩት ያለአግባብ ከአውዱ ውጪ ተላልፏል ባሉ ባለስልጣን አማካኝነት ዓርብ ዕለት የታሰረው ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ፍርድ ቤት አለመቅረቡም ታውቋል።

ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡን ወደ ኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮና ኦሮሚያ ፖሊስ ያደረግነው የስልክ ጥሪ ምላሽ አላገኘም።

የአሀዱ ሬዲዮ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሊዲያ አበበ ጉዳዩ ከመብት ጥሰት ባለፈ የስነልቦና ጉዳት የሚያደርስ ነው ብላለች።

በፌደራል መንግስት ፈቃድ አውጥተው የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን የሚጠየቁት በፌደራል መንግስት የጸጥታ እና የፍትህ ተቋማት  መሆኑን የሚገልጹት የህግ ባለሙያዎች የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ድርጊት ሕገ ወጥ ነው ሲሉ ተችተዋል።

ይህ ዓይነት አሰራር ከፍተኛ አፈና በነበረበት በቀደመው የሕወሃት ዘመን እንኳን ብዙም የሚያጋጥም እንዳልነበርም ለመረዳት ተችሏል።

የጦማር ዋና አዘጋጅ የነበረው በፍቃዱ ሞረዳ  እንዲሁም የፊያሜታ አዘጋጅ የነበረው ዳዊት ከበደ በቤንሻንጉል ክልል እና  በደቡብ ክልል ፖሊስ አሶሳ እና አዋሳ  ተወስደው የታሰሩበት ድርጊት በሕወሃት ዘመን የሚጠቀሱ ናቸው።