በቴፒ በነዋሪዎች ላይ የሚደርሰው እስርና ግድያ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 19/2011) በቴፒ በነዋሪዎች ላይ የሚደርሰው እስርና ግድያ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

ፋይል

ይህን ተከትሎም በአካባቢው ጭንቀትና ውጥረት መንገሱን ነው ነዋሪዎች ለኢሳት የገለጹት።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ምርመራ ቡድን በአካባቢው እንቅስቃሴ እየደረገ ቢሆንም ለውጡን ያልተቀበሉ አመራሮች እጃቸው በወንጀሉ ውስጥ መኖሩ ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።

በደቡብ ክልል ከፋ ዞንን ጨምሮ በሶስት ዞኖች ከመጋቢት 20 ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ነበር ይላሉ የቴፒ ነዋሪዎች።

ያንን ተከትሎም የፌደራሉ አቃቢ ህግ የምርመራ ቡድን በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልትና ስቃይ ለማጣራት ብሎም በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላትን ለህግ ለማቅረብ በአካባቢው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ይገልጻሉ ነዋሪዎቹ።

ነገር ግን በእያንዳንዱ ወንጀል ውስጥ ለውጡን የማይደግፉ አካላት እጅ መኖሩ ስራውን ከባድ አድርጎታል ባይ ናቸው ።

ከዚሁ ምርመራ ጋር ተያይዞም የዞኑ የፖሊስ አዛዥ ዛሬ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ይላሉ በአካባቢው ያለው ውጥረትና አለመረጋጋት ተባብሷል።ሰዎችን ይገደላሉ፣ይታሰራሉ ስቃዩ የከፋ ነው በማለትም ጭምር

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ይሁን እንጂ ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎችንም ሆነ የሚታየውን ችግር ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች አይታዩም ነው የሚሉት።

የሚመለከታቸው አካላትም ቢሆኑ ወደ አካባቢው መተውና በጉዳዩ ላይ ተወያይተው መፍትሄ ማምጣት አልቻሉም ብለዋል።