የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን በእሳት ጋየ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 4/2011)የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን በእሳት መጋየቱ ተሰማ።

የምርጫ ኮሚሽኑ ቃጠሎ በሃገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊካሄድ አንድ ሳምንት ብቻ በቀረበት በዚህ ሰአት መፈጸሙ አነጋጋሪ ሆኗል።

በናይጄሪያ ፕላቶ በተባለው ግዛት የሚገኘው የምርጫ ኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት በተነሳው ቃጠሎ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቁሶችና የድምጽ መስጫ ሳጥኖች ጭምር መውደማቸው ታውቋል።

ከ36ቱ የናይጄሪያ ግዛቶች አንዱ በሆነውና በሃገሪቱ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ በሚገኘው ፕላቶ ግዛት በምርጫ ኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ላይ የእሳት ቃጠሎ መነሳቱ ታውቋል።

የእሳት ቃጠሎውን ያደረሰው አካል ግን እስካሁን አለመታወቁን ነው ዘገባዎች ያመለከቱት።

የምርጫ ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አደጋው ድንገተኛ ይሁን የታቀደ ለጊዜው አለመታወቁን       ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ከወዲሁ ሴራ ነው ብሎ ለመደምደም እንደማይቻል መናገራቸውን ነው ቢቢሲ በዘገባው ያሰፈረው።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ በበኩላቸው የምርጫ መጭበርበር ስጋቶች መኖራቸውን አመልክተዋል።

የሐገሪቱ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ወንጀሎች ኮሚሽን የሕዝብ ድምጽ ለመግዛት ገንዘብ እየተረጨ መሆኑን በመግለጽ በምርጫው ላይ ያንዣበበውን ስጋት ጠቁሟል።

የፊታችን ቅዳሜ በናይጄሪያ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ የሚገኙት ሙሐመዱ ቡሃሪ ከቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት አቲኩ አቡባክር ከፍተኛ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው በመገለጹ ሒደቱ ከወዲሁ ውጥረት የተመላበት ሆኗል።

በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ቀዳሚ የሆነችው ናይጄሪያ 190 ሚሊየን ያህል ህዝብ የሚኖርባት ሲሆን ከዚህ ህዝብ ከ80 ሚሊየን በላይ የሚሆነው በምርጫው ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።