የሜቴክ ዋና ዳይሬክተርና የኢንሳ ዳይሬክተር በሌላ ተተኩ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 11/2010)የብሔራዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና የኢንሳ ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ ምትክ አዲስ ሰዎች መሾማቸው ተሰማ።የፖሊስ ኮሚሽነሩም በሌላ ሰው ተተክተዋል።

የብሔራዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ የሐገሪቱን ሃብት በመመዝበርና በማባከን በከፍተኛ ደረጃ እየተወቀሰ ሲሆን፣ ሃላፊዎቹም በበርካታ ቢሊዮን ብር ብክነት ተጠያቂ መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል።

ሹምሽሩ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረብ ይጨምራል ወይ የሚለውም እያነጋገረ ይገኛል።

ሁለቱ የሕወሃት ጄኔራሎች የስራ መልቀቂያ በፈቃዳቸው ማቅረባቸውን ለስርአቱ ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን ባለፈው ሳምንት ዘግበዋል።

የብሔራዊ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት /ኢንሳ/ ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በተባሉ ግለሰብ ተተክተዋል።የቅርብ ምንጮች እንደገለጹት አቶ ተመስገን በኢንሳ ውስጥ  በሻለቃ ማዕረግ በማገልገል ላይ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት ባልደረባ ናቸው።

ዛሬ ከንግድ ሚኒስትርነታቸው የተነሱት ዶክተር በቀለ ቡላዶ ደግሞ  ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ተክተው የሜቴክ ዳይሬክተር ሆነዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር  ጄኔራል አቶ አሰፋ አብዩ ተነስተው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ባልደረባ የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን እሳቸውን ተክተው መሾማቸው ተመልክቷል።

ከአፈጉባኤነት የተነሱት አቶ አባዱላ ገመዳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህነት ጉዳዮች አማካሪ ሆነው ሲሾሙ ፣የሕወሃት ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ደግሞ  በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ ሆነው ተሹመዋል።

ከሴቶችና የሕጻናት ጉዳይ ሚኒስትርነት የተነሱት ወይዘሮ ደሚቱ ሐምቢሳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

አቶ አህመድ አብተው አቶ አባይ ጸሓዬን ተክተው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ሲሆኑ አወዛጋቢው የብአዴኑ አመራር አቶ አለምነው መኮንን የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

አቶ ሞገስ ባልቻ ደግሞ የወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ረዳት ሆነው መሾማቸው ተመልክቷል።

የሐገሪቱ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ እንዲሁም የሀገሪቱ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ከግንቦት ወር 1993 ጀምሮ ላለፉት 17 አመታት በያዙት ስልጣናቸው ላይ የቀጠሉ ሲሆን፣ በተዋረድ ያለውም አመራርና መዋቅር በሕወሃት ታጋዮች ስር ቀጥሏል።

የብሔራዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ የሐገሪቱን ሃብት በመመዝበርና በማባከን በከፍተኛ ደረጃ እየተወቀሰ ሲሆን፣ ሃላፊዎቹም በበርካታ ቢሊዮን ብር ብክነት ተጠያቂ መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል።ሹምሽሩ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረብ ይጨምራል ወይ የሚለውም እያነጋገረ ይገኛል።