ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 28/2011)የኢትዮጵያ አየር ሃይል ተዋጊ ጀት አብራሪ የነበሩት ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

በ1969 ኢትዮጵያ በሶማሊያ በተወረረችበት ወቅት በአየር ላይ ውጊያ ሃገራቸውን ከታደጉ የበረራ ባለሙያዎች አንዱ የነበሩት ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ ለከፍተኛ ህክምና በተጓዙበት ህንድ ህይወታቸው ያለፈው በትናንትናው ዕለት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

በ1983 ዓም የኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ካባረራቸው የበረራ ባለሙያዎች አንዱ የነበሩት ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ በኤርትራ መንግስት ጥያቄ የኤርትራ አየር ሃይል ፓይለቶችን ለማሰልጠን ወደዚያ ከተጓዙ ኢትዮጵያውያን የበረራ ባለሙያዎች አንዱ ነበሩ።

ከዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ስርዓት ለመለወጥ በሚያደርገው ትግል ውስጥ በመሳተፍ የአርበኞች ግንባር  አመራር የነበሩት ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ተይዘው በኤርትራ ወህኒ ቤት ውስጥ ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በህመም ላይ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ በሃገር ቤት ያደረጉት የህክምና ጥረት ባለመሳካቱ የውጭ ህክምና ለማግኘት በተጓዙበት ህንድ ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።