የብሔራዊ እርቅና ሰላም እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽኖች አባላት ሹመት ጸደቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 28/2011)የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የብሔራዊ  እርቀ ሰላም ኮሚሽን  እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች አባላትን ሹመት አጸደቀ።

ሹመቱ ፖለቲከኞች፣ የሀይማኖት እባቶችን እና ታዋቂ ሰዎችን ያካታተ ነው።

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላትን ለማጽደቅ በተሰጠው ድምጽ 22 ታቃውሞና 4 ድምጸ ታእቅቦ ተመዝግቧል።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የቀረቡ 40 እጩ አባላትን ሹመት በ22 ተቃውሞና በ4 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁ ተሰምቷል።

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት በኢትዮጵያ የግጭት መንስኤ የሆኑ የወሰን እና የማንነት ጉዳዮችን በማጥናት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፌዴሬሽንና ለተወካዮች ምክር ቤቶች ምክረ ሀሳብ የሚያቀርቡ ናቸው።

በዚሁም መሰረት የኮሚሽኑ አባላት ከፖለቲከኞች፣ ከምሁራን እና ከታዋቂ ሰዎች የተወጣጡ ናቸው፡፡

ከአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት መካከል የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ ፖለቲከኛና የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ዶክተር አረጋዊ በርሔ ፖለቲከኛ፣ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና – ፖለቲከኛ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፖለቲከኛ፣ አቶ ሌንጮ ለታ ፖለቲከኛ ተካተውበታል።

ከታዋቂ ሰዎችና ከምሁራን መካከል ደግሞ አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ጋዜጠኛ ወይዘሮ መዓዛ ብሩ፣ዶክተር መስፍን አርአያ – በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ፣ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ  ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ዶክተር መስፍን አርአያ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያና  ኡስታዝ አቡበክር አህመድ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ምክር ቤቱ የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን 41 አባላትን ሹመት አጽድቋል።

በዚህም መሰረት የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት የሃይማኖት አባቶች፥ ፖለቲከኞችና እና ታውቂ ሰዎች ሆነው ተሹመዋል።

ከነዚሁም መካከል ብፁእ አቡነ አብርሃም – ከኦርቶዶክስ ፥ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ- ከካቶሊክ፣ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ኡመር ኢድሪስ- ከእስልምና፣ ዶክተር ቤተ መንግስቱ – ከወንጌላዊያን፣ ፓስተር ተስፋዬ ጋቢሶ ከወንጌላዊያን የኮሚሽኑ አባል ሆነዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ዶክተር ብርሃኑ ነጋ – ፖለቲከኛ፣ፕሮፌሰር በየነ ዼጥሮስ ፖለቲከኛ፣ዶክተር ግደይ ዘርዓጺዮን ፖለቲከኛ፣ ከምሁራን ዶክተር ምህረት ደበበ ከሀሳብ መሪዎች፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ – የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ – ከታዋቂ ሰዎች መካከል ይገኙበታል።