ከአራት ዓመታት በፊት የዓለምአቀፍ ሕግን በሚጻረር መልኩ ከየመን ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ታግተው የተወሰዱት የነፃነት ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር እንደተፈቱ በስፋት ቢነገርም ከመንግስት፣ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ዘንድ ማረጋገጥ አልተቻለም።

ከአራት ዓመታት በፊት የዓለምአቀፍ ሕግን በሚጻረር መልኩ ከየመን ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ታግተው የተወሰዱት የነፃነት ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር እንደተፈቱ በስፋት ቢነገርም ከመንግስት፣ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ዘንድ ማረጋገጥ አልተቻለም።
(ኢሳት ዜና ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ/ም) አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በህገወጥ መንገድ ከታገቱበት ጊዜ አንስቶ በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞ ሰልፎችና በተለያዩ መድረኮች ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። ከዚህም ባሻገር አንዳርጋቸውን ለማስለቀቅና እርሳቸው የታሰሩለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ በተደረገ ትግል የህይወት መስዋዕት ድረስ የከፈሉ ጥቂቶች አይደሉም።
ከሳምንት በፊት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቤተመንግስት ባደረጉት ንግግር አንዳርጋቸው በመታሰሩ መንግስታቸው ከጉዳት በስተቀር ያገኘው ጥቅም እንደሌለ በመጥቀስ የነጻነት ታጋዩ በተያዘው ሳምንት እንደሚፈታ መናገራቸው ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስተው እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተስፋ ሲጠባበቁ ሰንብተዋል። በተለይ እንዲፈታ መወሰኑ ከተነገረበት ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ በየእለቱ ቃሊቲ ድረስ በመጉረፍና በመኖሪያ ቤቱ በመታደም በከፍተኛ ጉጉትና ደስታ ባረገዘ ምጥ ሲጠብቀው ቆይቷል።
የኢሳት ወኪሎች ከአዲስ አበባ እንደዘገቡት በዛሬው ዕለት ለአንዳርጋቸው አቀባበል ለማድረግ ብዛት ያላቸው ታክሲዎችና የቤት መኪናዎች በቃሊቲ የተገኙ ሲሆን፣ ከተማው የአንዳርጋቸው ምስል ያለበትን ቲሸርት በለበሱ ወጣቶች ተሞልቶ ውሏል።
ነገረ ፍችው ከተሰማበት ጊዜ አንስቶም ለአቀባበሉ ግብረኃይል ያቋቋሙ የመዲናዋ ወጣቶች የወላጆቹን ቤት በማድመቅ፣ ቲሸርት በማሳተምና የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ሲደክሙ የሰነበቱ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ በወላጆቹ መኖሪያ ቤት ላይ “የመርህ ሰው” በሚል ርዕስ ምስሉን በትልቁ ሰቅለዋል።
በዛሬው ዕለት ሕዝቡ በከፍተኛ ስሜት ሆኖ በቃሊቲ በር ላይ እየተጠባበቀ ባለበት ጊዜ ከእስር ቤቱ ውስጥ በጥቁር መስተዋት የተሸፈኑ ወደ አምስት የሚሆኑ “ቪ8″ መኪናዎች በከፍተኛ ፍጥነት ወጥተው የተጓዙ ሲሆን፣ በስፍራው የነበሩ ኢትዮጵያውያን የነጻነት ታጋዩ አንዳርጋቸው ጽጌ በአንድኛው መኪና ውስጥ ሆነው ሳይወጡ እንዳልቀሩ ገምተዋል። ይሁንና በርካቶች በመኪና ሆነው መኪኖቹን ቢከታተሏቸውም በመገናኛ አቅጣጫ በመክነፍ ወዳልታወቀ ቦታ ተሰውረዋል። ከዚያም በርካቶች በወላጆቹ ቤት በከፍተኛ ጉጉት ለረዥም ሰዓታት ቢጠብቁም የነጻነት ታጋዩን ብቅ ሊል አልቻለም።
በሁኔታው የተበሳጩ ብዙ ሰዎች” አንዳርጋቸውን ሳናዬውና አቅፈነው ደስታችንን ሳንገልጥ ወደ እንግሊዝ ሊልኩብን ነው” በማለት ቅሬታ ሲያሰሙ ውለዋል።
ከአሁን አሁን አንዳርጋቸው ወደ ወላጆቹ ቤት ሊመጣ ይችላል በሚል ተስፋ ቦሌ ወደሚገኘው ወደ ቤተሰቦቹ ቤት የሚወስደው መንገድ በመኪና ጡሩምባ ደምቆ ውሏል። ከቀትር በኋላ እጅግ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች በወላጆቻቸው መኖሪያ ቤት በመገኘት ስሜታቸውን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው ድረስ ደስታቸውን በሆታና በጭፈራ ሲገልጹ ውለዋል።በርካቶች ወደ ዝግጅት ክፍላችን በመደወል ፣ ሌሎች ደግሞ በጽሁፍ አስተያዬታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
እናት እናትዬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ “ክብር ይሄን ጀግና ወልደው ለእኛ ላበረከቱልን ወላጆቹ!!፣ክብር አላማውን ደግፈው ለሚያበረታቱት ፈርተው ወይ ሳስተው ወደኋላ ላልጎተቱት ከጎኑ ለቆሙት ታላቅ ታናሽ እህት ወንድሞቹ!!!ክብር ናፍቆት እያንገበገባቸው ፍቅሩ እየራባቸው እቅፉ እየናፈቃቸው ወደ በርሃ ለሸኙት ባለቤቱ እና ልጆቹ!!!!ክብር እሱ የጀመረውን ከግብ ለማድረስ በአላማ ፅናት ሙቀት ብርዱን ችለው የጠላት በትርን ተቋቁመው በፅናት ለሚጠብቁት ጓዶቹ!!! ክብር ከተያዘባት ቀን አንስቶ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ህመሙን ህመማቸው ስቃዩን ስቃያቸው አድርገው ሌት ተቀን ስለሱ ለሚዋትቱ ቀን ለሚቆጥሩ የመንፈስ ልጆቹ!!! ክብር ለተገፋው ለተጨቆነው ፍትህ ለተጠማው ነፃነት ለናፈቀው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ብለዋል።