አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ምህዳሩ መዘጋቱን ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 5/2011)በኢትዮጵያ በየክልሉ ያሉ የኢህአዲግ መዋቅር አባላት ከቀደመው ስርዓት በከፋ መልኩ ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ምህዳሩን እንደዘጉት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ገለጹ።

አቶ አንዳርጋቸው ከጀርመን ድምጽ ራዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ዶክተር አብይ ስልጣን እንደያዙ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ቢጀምርም የኢህአዴግ መዋቅር የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ድርጅቶችን በጠላትነት ፈርጀው እንቅስቃሴያቸውን ገድበዋል ብለዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዳሉት ዘርን እና ቋንቋን ማዕከል ያደረገው ስርዓት ሀገሪቱን ወደ ጥፋት እያመራት ነው።

አንደ እርሳቸው ገለጻ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ከመብት ጥሰት የሚያላቅቅ ቢመስልም አሁንም ኢትዮጵያን የሚያሳጣ የከፋ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።

እናም ማንም አሸናፊ ወደ ማይኮንበት ችግር እንገባለን ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስጠንቅቀዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደገለጹት የሃገሪቱ ፖለቲካ በጊዜ ገደብ ካልተበጀለት በስተቀር ከፍተኛ ጥፋት ያስከትላል።ለዚህ ደግሞ ዋነኛው መዘዙ የዘር ፖለቲካው ነው ብለዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አሁን በስልጣን ላይ ያሉ አካላት አሁን ባለው የፌደራል ስርአት አንደራደርም ማለታቸው  አግባብ አይደለም ሲሉም ተችተዋል።

መንግሥት ካለው ጉልበት በላይ በፌደራሊዝም ሥርዓት ስም የራሳቸውን የደህንነት መዋቅር፥ ወታደራዊ ኃይል እና በዘር ላይ የተመሰረተ ሚዲያ ያደራጁ የክልል አስተዳደሮች በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ላይ ትልቅ ማነቆ መፍጠራቸውን ነው የገለጹት። –ከጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልልስ።

በትግራይ ብቻ 1.2 ሚሊዮን ታጣቂዎች መኖራቸውንና በዘር ላይ የተመሰረቱ ሚዲያዎች ተይዞ ጤናማ የፌዴራል ስርአት ግንባታ አለ ብሎ ለማለትም አዳጋች ነው ብለዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዳሉት ዶክተር አብይ ስልጣን እንደያዙ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ቢጀምርም በየክልሉ የሚገኙ የኢህአዴግ አባላት ከቀደመው ሥርዓት በከፋ መልኩ ሙሉ ለሙሉ የፖለቲካ ምህዳሩን ዘግተውታል።

እነዚህ አባላት የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ድርጅቶችን በጠላትነት ፈርጀው እንቅስቃሴያቸውን ገድበዋል ሲሉም ነው የገለጹት።

በዚህ የተነሳም የሕብረተሰቡም ሆነ የአገሪቱ ህልውና በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ አደጋ እና ስጋት ውስጥ ወድቋልም ብለዋል::

እናም በሃገር ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመሻገር ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች ያሳተፈ  ሕዝባዊ የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅና እንዲመቻች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጥሪ አቅርበዋል።