አቶ ታደሰ ካሳ እንዲከሰሱ ከተወሰነ በኋላ ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 10/2011) በቅርቡ ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የታገዱት አቶ ታደሰ ካሳ በከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው እንዲከሰሱ ከተወሰነ በኋላ ሂደቱ በእጅ አዙር እንዲቋረጥ ተደርጎ መቆየቱን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

አቶ ታደሰ ካሳ ወይንም ታደሰ ጥንቅሹ በመባል የሚታወቁት የብአዴን መስራች የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም/አብቁተ/ን ሲመሩ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ለሞቱ ቤተሰቦች ካሳ ተከፍሏል በሚል ያለ ማወራረጃ ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸው በኦዲት ተረጋግጧል።

በዚሁ ምክንያት በከፍተኛ ሙስና የተጠረጠሩት አቶ ታደሰ ካሳ በፖሊስ ምርመራ ከተደረገ በኋላ እንዲከሰሱ ቢወሰንም ባልታወቁ ስውር እጆች ክሱ መቋረጡን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም/አብቁተ/ን ለረጅም ጊዜ የመሩት የብአዴኑ ታጋይ አቶ ታደሰ ካሳ በቅርቡ በኤፈርት ተፈጸመ ከተባለ ስርቆት ጋር በተያያዘ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት መታገዳቸው ይታወሳል።

ከዚሁ ስርቆት ጋር በተያያዘ እንዲሁም የአማራ ሕዝብን ጥቅም አላስከበሩም የተባሉት አቶ በረከት ስምኦንም ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት በተመሳሳይ ሁኔታ መታገዳቸው ይታወቃል።

ሁለቱም ነባር ታጋዮች ክሱን ቢያስተባብሉም በተለይም በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተፈጽሟል በሚል የተጀመረ ምርመራና ክስ ባልታወቁ ሰዎች እጅ እንዲቋረጥ ተደርጎ መቆየቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ወደ 30ሺ የሚጠጉ የአማራ ክልል ተወላጆች ሞተዋል በሚል ወደ እያንዳንዳቸው ቤተሰቦች በነፍስ ወከፍ 20ሺ ብር እንዲከፈል በፌደራል መንግስት ተወስኖ ነበር።

ይህም ገንዘብ ከፌደራል መንግስት በጀት ተመድቦ በአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም/አብቁተ/በኩል እንዲከፈል ተወስኖ ገንዘቡ ተከፍሏል በሚል ከፍተኛ ሙስና መፈጸሙ ነው የተነገረው።

የኢሳት ምንጮች እንዳሉት ገንዘቡ ስለመከፈሉ በሰነድ የተረጋገጠው 7ሺ ለሚሆኑት ብቻ ነው።

ከ23 ሺህ ብር በላይ የጦር ጉዳተኞች ቤተሰቦች ገንዘቡ ለእያንዳንዳቸው 20ሺ ብር ተከፍሏል ቢባልም የሒሳብ ማረጋገጫ ሰነድ በኦዲት ተከፍሏል ቢባልም የሒሳብ ማረጋገጫ ሰነድ በኦዲት አለመገኘቱን በወቅቱ ለማረጋገጥ ተችሎ ነበር።

እናም ጉዳዩ በፖሊስ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ የቀድሞው የብአዴን አመራርና የአብቁተ ሃላፊ አቶ ታደሰ ካሳ በአቃቤ ሕግ እንዲከሰሱ ከተወሰነ በኋላ ሂደቱ ባልታወቁ ሰዎች እንዲቋረጥ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ከ70ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ይታወሳል።

ከነዚህም ውስጥ ወደ 30ሺ የሚጠጉ የአማራ ተወላጆች በጦርነቱ ተገድለዋል በሚል የጉዳት ካሳ እንዲከፈል መወሰኑ ይነገራል።

በጉዳይ ካሳ ስም ለአማራ ጉዳተኛ ቤተሰቦች ገንዘቡ ይሰጣል ቢባልም ከ4 መቶ ሚሊየን ብር በላይ በእነ አቶ ታደሰ ካሳ መበላቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በዚሁም መሰረት በሕወሃት ተልዕኮ ፈጻሚነታቸው በሚታወቁት የተወሰኑ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንደገና ለማንሰራራት እየሞከሩ መሆናቸው ተነግሯል።

ከነዚሁ አመራር አባላት መካከል አቶ ከበደ ጫኔ፣አቶ ጌታቸው አምባዬ፣አቶ ለመነው መኮንንና ወይዘሮ ዝማም አሰፋ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲወገዱ በሕዝቡ ግፊት እየተደረገ ይገኛል።

የብአዴን ጉባኤ ከመስከረም 17-19/2010 ድረስ በባህርዳር ከመካሄዱ በፊት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲሁም የለውጥ አደናቃፊዎቹ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲታገዱ ሕዝቡ እየጠየቀ ይገኛል።