አርበኛ መሳፍንት ተስፉ የተደረገላቸው አቀባበል ከጠበቁት በላይ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 12/2011) በጎንደርና በዳባት የተደረገላቸው አቀባበል ከጠበቁት በላይ እንደሆነባቸው አርበኛ መሳፍንት ተስፉ ገለጹ።

አርበኛ መሳፍንት ከኢሳትጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት የህዝብ ስሜት የከፈሉት መስዋዕትነት ዋጋ እንዳለው ያሳየ ሆኗል።

ከ250 ጦራቸው ጋር ከጎንደር በኋላ ወደ ባህርዳር የገቡት አርበኛ መሳፍንት ተስፉ ነጻነትና ፍትህ እስኪረጋገጥ በትግላቸው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ከመንግስት ጋር ስምምነት ላይ የደረሱባቸውን ጉዳዮች ወደፊት በዝርዝር እንደሚገልጹና አሁን ባለው ለውጥ ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ከ2008 ዓም ጀምሮ ቤቱ ጫካ፣ ኑሮው ትግል፡ ሆኖ ቆይቷል።

የጎንደር ዱርና ገደል የዚህን አርበኛ የነጻነት ታጋይ የጎበዝ አለቃ ጀግንነት መስክረዋል።

የህወሃትን አገዛዝ መውጪያና መግቢያ በማሳጣት የነጻነት ተጋድሎው በድል እንዲጓዝ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍለዋል።

ብረት እንዲያነሱ፣ አገዛዙን በሃይል ለመጣል የጫካውን መንገድ እንዲመርጡ ያደረጋቸው በህዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል ነበር።

በእሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ የደረሰው መከራም ለትግል በረሃ እንዲወጡ  አድርጓቸዋል። አርበኛ የነጻነት ፋኖ፣የጎበዝ አለቃ መሳፍንት ተስፉ።

ከ2008 ዓመተምህረት ጀምሮ ላለፉት ሶስት ዓመታት የጎንደር ጫካ ተራራና ገደሉ ከአርበኛ መሳፍንት ተስፉ ተጋድሎ ጋር ሲነሱ ቆይተዋል።

በዘመናዊ መልክ የተደራጀውንና እስከአፍንጫው የታጠቀውን የህወሃት አገዛዝ ሰራዊትን በየአውደ ውጊያ ድል እየመቱ ህዝቡን ለትግል በማነሳሳትና ለህወሃት አገዛዝም ራስ ምታት በመሆን ዘልቀዋል።

አርበኛ መሳፍንት በየከተሞቹ ለሚደረጉት ህዝባዊ ንቅናቄዎች የሞራል ምርኩዝ፣ የወኔ ማነቃቂያ ድሎችን እያስመዘገቡ በቆዩባቸው በእነዚህ ዓመታት በህወሃት አገዛዝ በኩል ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል።

ሰርጎ ገብ በመላክ አፍኖ ለመያዝ የተደረጉ በርካታ የህወሃት አገዛዝ ሴራዎችን በመበጣጠስ በድል አድራጊነት ቆይተዋል።

ለእኚህ አርበኛና የነጻነት ታጋይና ለጦራቸው ዳባትና ጎንደር የጀግና አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ከትላንት በስቲያ ጀምሮ ጎንደርና ዳባት ጀግኖቹን ለመቀበል ከፍተኛ ዝግጅት አድርጓል።

ከራያ ድረስ በርካታ ታጣቂዎች ጎንደር ገብተዋል። አቀባበሉ ልዩ ነበር፣ ከጠበኩት በላይ ነው ይላሉ አርበኛ መሳፍንት ተስፉ።

አርበኛ መሳፍንትና ጦራቸው ከአማራ ክልል መንግስት ጋር በተደረገ ስምምነት ወደ ህዝብ መቀላቀላቸው ተገልጿል።

ጎንደርና ዳባት በከፍተኛ አቀባበል የቆዩት ታጋዮቹ ዛሬ ባህርዳር መግባታቸው ታውቋል። አርበኛ መሳፍንት ለውጡ ገና ነው ብዙ ትግል ይጠይቃል ይላሉ።