ተመድ 10 ሺ ለሚሆኑ ከሞያሌ ከተማ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

ተመድ 10 ሺ ለሚሆኑ ከሞያሌ ከተማ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 12 ቀን 2010 ዓ/ም) ራሱን ኮማንድ ፖስት በሚል የሚጠራው ወታደራዊ እዝ በበኩሉ ተፈናቃዮች እየተመለሱ ነው ብሎአል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽነር ከኬንያ ባወጣው መረጃ ከኢትዮጵያዋ የሞያሌ ከተማ ለተፈናቀሉ 10 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች ዛሬ የቤትና የምግብ ማብሰያ እቃዎችን ሲያድል መዋሉን ገልጿል።
ወታደራዊ እዙ ባወጣው መግለጫ ደግሞ በኦነግ የተሳሳተ ወሬ ወደ ኬንያ ከተሰደዱት 7 ሺ 800 የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አብዛኞቹ ወደ ወደቀያቸው እየተመለሱ ነው ብሎአል። ወታደራዊ እዙ አንዳንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የሚዲያ ተቋማት መሰረተ ቢስና ከእውነት የራቀ ወሬ በማሰራጨት ላይ በመሆናቸው ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ካልተቆጠቡ ግን አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግሯል።
ተመድ በፎቶ አስደግፎ ባወጣው መረጃ ዛሬ 10 ሺ የሚሆኑ ዜጎች እርዳታ ሲቀበሉ መዋላቸውን አረጋግጧል። የተመድ መግለጫ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ስለመመለሳቸው ምንም የገለጸው ነገር የለም። ወታደራዊ እዙ የጠቀሰው የተፈናቃዮች አሃዝም ከተመድ መግለጫ ጋር አይገናኝም።
የሚዲያ አካላት በአብዛኛው ተመድን በመጥቀስ ዘገባዎችን እያቀረቡ ሲሆን፣ ወታደራዊ እዙ በተመድ ላይ ክስ ለመክፈት ይሞክር አይሞክር የታወቀ ነገር የለም።
የአገዛዙ ወታደሮች በሞያሌ ከተማ ህዝብ ላይ በከፈቱት ጥቃት 13 ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል። ይህን ተከትሎ ከ10 ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል። የወታደራዊ እዙ መሪዎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት በስህተት እርምጃ መውሰዳቸውን ጠቅሰው ይቅርታ ጠይቀው ነበር። ይሁን እንጅ ሰሞኑን ደግሞ የተፈናቀሉት ሰዎች የኦነግን ቅስቀሳ በመስማት ነው የሚል አዲስ ቅስቀሳ ጀምረዋል።