ብ/ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና የአጋዚ ክፍለ ጦር አዛዥ ሆኑ

ሰኔ ፪ ( ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የምስራቅ እዝ ምክትል አዛዥ የነበሩት ብ/ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና የአጋዚ ክፍለ ጦር አዛዥ ሆነው ሲሸሙ ጄል ገብረመድህን በቅጽል ስማቸው ወዲ ነጮ ደግሞ ምክትል ሆነዋል።
ብ/ ጄኔራል ጌታቸው በኦሮምያ ከነበረው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ግምገማ ቀርቦባቸው ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ በጭካኔውና በፈጸማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚታወቀውን የአጋዚ ክፍለጦር እንዲመሩ መደረጉ በጄኔራሉ ላይ ቅሬታ መፍጠሩን ምንጮች ይናገራሉ። በተለይ በጭካኔያቸው ተወዳዳሪ የላቸውም የሚባሉትን ወዲ ነጮን ከእርሳቸው ስር በማድረግ እና ትእዛዞች ሁሉ በእርሳቸው በኩል እንዲሰጡ በማድረግ ጄ/ል ጌታቸውን በህዝብ በማስጠላት በመጨረሻ ለማስወገድ የታቀደ ሴራ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች አስተያየታቸውን ገለጸዋል። ብ/ጄኔራል ጌታቸው አዋሳ ወደሚገኘው የአጋዚ ማዘዣ ጣቢያ እንዲዛወሩ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ ለሰራዊት የሚመለመሉ ወጣቶች አለመገኘታቸውን ተከትሎ፣ የመከላከያ ባለስልጣናት የተለያዩ ማባበያዎችን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ናቸው። ወጣቶችን በተለያዩ የትምህርት እድሎች በመደለልና የገንዘብ ስጦታ በመስጠት ወደ መከላከያ እንዲገቡ ለማድረግ እቅዶች መኖራቸውን ምንጮች ገልጸዋል።