የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ስራአስኪያጅ አባ ሃይለማርያም የመመረቂያ ጽሁፋቸውን ከሌላ ተማሪ ጽሁፍ ገልብጠው የዶክትሬት ዲግሪ እንዳገኙ ተጋለጠ

ሰኔ ፪ ( ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ስራ አስኪያጅ፣ የአለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ የስራ አስፈጻሚ አባልና በቅርቡ ደግሞ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት “ዕጩ ቆሞስ” ኾነው የተሾሙት አባ ሃይለማርያም መለሰ ፣ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 ለደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ባቀረቡት የዶክትሬት የመመረቂያ ጽሀፍ ላይ ፣ ከዚህ ቀደም በአንድ ኢትዮጵያዊ ቄስ የተጻፈውን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ገልበጠው መመረቃቸውን ኢሳት ለማረጋገጥ ችሎአል።
በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን እንዳላቸው የሚነገርላቸውና ገዢው ፓርቲ በቤተክርስቲያኑዋ ውስጥ ለሚፈጸመው ወንጀሎች ዋና ተባባሪ ተደርገው ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚቀርብባቸው አባ ሃይለማርያም መለሰ አየነው፣ ለደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ( UNISA) Influence of Cyrillian Christology in the Ethiopian Orthodox Anaphora በሚል ርእስ ያቀረቡት የመመሪቂያ ጽሁፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተገለበጠው ቀሲስ መብራቱ ኪሮስ Ethiopian Christology በሚል ርዕስ ለ Toronto School of Theology and the University of St. Micheal’s College in the University of Toronto ለማስተርስ ዲግሪያቸው መመረቂያ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2005 ካቀረቡት ጽሁፍ ላይ ነው።
ኢሳት የሁለቱን ሰዎች የመመረቂያ ጽሁፍ በጥለቅት ካመሳከረ በሁዋላ፣ አባ ሃይለማርያም ከገጽ 36-47 ፣ ከ181-185፣ 186-217፣ 218-225፣ 265-268፣ 268-271፣ 271-273፣ 273-278፣ 278-291 ያሉት ጽሁፎች በሙሉ የቃል ለውጥ እንኳን ሳይደረግ ከቀሲስ መብራቱ የመመረቂያ ጽሁፍ ላይ ተገልብጠው መወሰዳቸውን አረጋግጧል። በጉዳዩ ዙሪያ በኢሜል ጥያቄ ያቀረብንላቸው ቀሲስ መብራቱ ፣ “ ጽሁፌ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ተገልብጦ መወሰዱን እንዳየሁ ለደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ኢሜል ጽፌአለሁ። አባ ሃይለማርያም የፈጸሙትን ድፈረት የተሞላበት የአካዳሚክ የስነ ምግባር ጥሰት በተጨባጭ ማስረጃ እንዳቀረብኩ ዩኒቨርስቲው የዶክተራል የመመረቂያ ጽሁፉን ከድረገጹ ላይ እንዲነሳ አድርጓል። ዩኒቨርስቲውም ለተጨማሪ ምርመራ እንደሚያነጋግራቸውና የዲሲፕሊን እርምጃ
እንደሚወስድባቸው አሳውቆኛል።” በማለት መልሰውልናል። አባ ሃይለማርያምን ከኢሳት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “ስለሚባለው ነገር አላውቅም” የሚል መልስ የሰጡን ሲሆን፣ የማብራሪያ ጥያቄ ስንጠይቃቸው ስልኩን ዘግተውብናል። ተመልሰን ለጸሃፊያቸው ብንደውልም፤ ጸሃፋያቸው ከእንግዳ ጋር መሆናቸውን በመግለጽ ልናገኛቸው እንደማንችል ነግረውናል።
ለደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲም እንዲሁ በኢሜል ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን፣ ዩኒቨርስቲው ይህን ዘገባ እሳከቀረብንበት ጊዜ ደረስ መልስ ሊሰጠን አልቻለም። ለወደፊቱ መልስ የሚሰጠን ከሆነ መልሱን ይዘን እንቀርባለን። የአገር ስብከቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ አባ ሃይለማርያም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያንን በአለማቀፍ የአብያተክርስቲያናት ጉባኤ ይወክላሉ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን ቴሌቪዥን እየቀረቡም መንፈሳዊ ትምህር ይሰጣሉ።
በቅርቡ ደግሞ አባ ሃይለማርያም የሰሜን ጎንደር እጩ ቆሞስ ኾነው መሾማቸውን ተከትሎ ምዕመናን በማህበራዊ ሚዲያ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው። የሰሜን ጎንደር አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሆኑት አቡነ ኤልሳዕ ግንቦት30 ቀን 2009 ዓም ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በጻፉት ደብዳቤ ” የዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ፣ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት መመደብ፣ ፈቃዳቸውና ምርጫቸው ያልተጠየቀበትና የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ” ይጻረራል ብለዋል። አስተያታቸውን እንዲያካፍሉን የጠየቅናቸው መምህር ዘመድኩን በቀለ በበኩላቸው የአባ ሃይለማርያም የሰሜን ጎንደር ሹመት ፖለቲካዊ ይዘት አለው ይላሉ።
ገዢው ፓርቲ በአቡነ ኤልሳዕ በኩል ጫካ ገብተው ለመብታቸው እየታገሉ ያሉትን የነጻነት ታጋዮች አግባብቶ ትግላቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ያደረገው ሙከራ መክሸፉ ፣ አቡኑን እንደልብ በሚታዘዙት በአባ ሃይለማርያም ለመተካት እንዳነሳሳው መምህር ዘመድኩን ያምናሉ።
ቤተክርስቲያኑዋ አሁንም ለአባ ሃይለማርያም የዶክትሬት ዲግሪ እውቅና በመስጠት ዶ/ር ብላ እንደምትጠራቸው ከደብዳቤ ልውውጦች ማረጋገጥ ተችሎአል። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከተለያዩ የሃሰት ዩኒቨርስቲዎች ዲግሪዎችን እንደሚገዙ ቢታወቅም፣ በሃይማኖት አባቶች ደረጃ ፣ ሌሎች በብዙ ድካም የጻፉዋቸውን ጽሁፎች ስነምግባር በጎደለው መልኩ ገልብጠው የራሳቸው ስራ አድርገው በማቅረብ የሃሰት የትምህርት ማስረጃ ሲያገኙ አባ ሃይለማርያም መለሰ የመጀመሪያው ሳይሆኑ አይቀርም።