ባሻ ጥጋቡ ተገኝ አረፉ

መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 
ኢሳት ዜና:-የሱዳንና የኢትዮጵያ ድንበር በተካለለበት ወቅት መሬታቸውን ለሱዳን እንዲያስረክቡ ሲጠየቁ አሻፈረኝ ብለው የቆዩት የምእራብ አርማጭሆ ወረዳ ባለሀብት ባሻ ጥጋቡ ተገኝ መጋቢት 10፣ 2005 ዓም አርፈዋል። የባለሀብቱ የቀብር ስነስርአት በላይ አርማጭሆ ካን ተንታ ቀበሌ መጋቢት 13 ቀን 2005 ተፈጽሟል። የአካባቢው ባለሀብቶች መሬታቸውን ለሱዳን መንግስት ሲያስረክቡ ፣ ባሻ ጥጋቡ ግን ” የአገሬን መሬት አሳልፌ አለሰጥም” በማለት ከባለስልጣን ጋር እየተወዛገቡ እስከ እለተሞታቸው ድረስ መሬቱን ሳያስረክቡ ቆይተዋል።
የአሟሟታቸው ሁኔታ ግልጽ አለመሆኑን የተናገሩት ግለሰቡን የሚያውቁት ሰዎች፣ ባለሀብቱ ባለፈው ሳምንት በሙሉ ጤንነት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ለኢሳት ገልጸዋል።
የ43 አመቱ ጎልማሳ ባለሀብት የአንድ ወንድ ልጅ እና የሁለት ሴት ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን፣ ለሱዳን በተሰጠው መሬት የተነሳ ህብረተሰቡን ታነሳሳለህ ተብለው በገዢው ፓርቲ ሰዎች ሲዋከቡ ቆይተዋል።