በድሬዳዋ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 14/2010) የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ዒሌ ከስልጣን እንዲወርድ በመጠየቅ በድሬዳዋ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ።

በከተማዋ ሶስት ቀበሌዎች በተካሄደው በዚሁ ተቃውሞ አብዲ ዒሌ በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቅ ተጠይቋል።

በሶማሌ ክልል ወጣቶች የተጀመረው ተቃውሞ በድሬዳዋ ቀጥሎ አብዲ ኢሌ ከሌላው የኢትዮጵያ ወገናችን ጋር ለማጋጨት እየፈጸመ ያለውን ሴራ እናወግዛለን የሚሉ መልዕክቶች የተሰሙበት መሆኑ ታውቋል።

ሶማሌ ክልል የተጀመረው ተቃውሞ የአብዲ ዒሌን ከስልጣን መውረድ በመጠየቅ ቀጥሏል።

በሽንሌ ተጀምሮ 11ዱንም ዞኖች ያዳረሰው ተቃውሞ ለሁለት ወራት ያዝ ለቀቅ እያደረገው የቀጠለ ሲሆን በድሬዳዋ በተከታታይ በመካሄድ ላይ ነው።

ትላንት ድሬዳዋ በአብዲ ዒሌ ላይ ውግዘት የሚያሰሙ የተቃውሞ መልዕክቶች ሲሰሙባት እንደነበረ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በተለይም በሶስት የድሬዳዋ ቀበሌዎች የተካሄደው ተቃውሞ ለአብዲ ዒሌ አመራር ግልጽ መልዕክት የተላለፈበት መሆኑን በቪዲዮ ከተደገፈው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የሶማሌ ክልል ወጣቶች በርባራታ በሚል የሚታወቁ ሲሆን በክልሉ የፍትህና ሰላም እጦት ዋናው ተጠያቂ ፕሬዝዳንቱ አብዲ ዒሌ መሆኑን በመግለጽ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ታውቋል።

ኢሳት ያነጋገራቸው ወጣቶች  አብዲ ዒሌ ስልጣኑን ለማስጠበቅ በሶማሌ ተወላጆች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር እያሴረ በመሆኑ የፌደራል መንግስት አስቸኳይ ርምጃ እንዲወስድ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ከሌላው የኢትዮጵያ ወገኑ ጋር አብሮ መኖር የሚፈልገውን የሶማሌ ክልል ህዝብን ለግል ስልጣኑ ማራዘሚያ በማስፈራሪያነት ይዞ እንገነጠላለን የሚለውን የፕሬዝዳንቱን አደገኛ መልዕክት እንደሚያወግዙትም ወጣቶቹ በተቃውሞ ሰልፋቸውን ላይ አንስተዋል።

አብዲ ዒሌ ከስልጣን ወርዶ ለፍርድ እንዲቀርብም ጠይቀዋል።

ላለፉት 10 ዓመታት የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በመሆን የዘለቁት አብዲ መሀመድ ዒሌ ከህወሀት ወታደራዊ አዛዦች ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር ቀጠናውን የቀውስ አድርገውታል የሚለው ክስ በተደጋጋሚ ይነሳል።

የኮንትሮባንድ ንግዱን ተቆጣጥረው የያዙት የህወሀት ጄነራሎች የአብዲ ዒሌ ከስልጣን መነሳትን እንደማይፈልጉ የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

ለአቤቱታ አዲስ አበባ የሚገኙትን የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችን በማዋከብና በማስፈራራት ላይ የሚገኙት የህወሀት ደህንነቶች ከአብዲ ዒሌ ጋር ተስማምታችሁ ካልሰራችሁ ትታሰራላችሁ እንዳሏቸው መዘገባችን ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት ከሽማግሌዎቹ መሃል 5ቱ ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን ዜና በኢሳት መቅረቡን ተከትሎ በያዝነው ሳምንት ውስጥ መፈታታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በድሬዳዋው የተቃውሞ ሰልፍ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት አብዲ ዒሌ በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲነሳ መጠየቁን ነው የደረሰን መረጃ ያመለክተው።