በካናዳ ቶሮንቶ አንድ እቃ ጫኝ መለስተኛ ተሽከርካሪ ባደረሰው አደጋ 10 አካል ጉዳተኞች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 15/2010) በካናዳ ቶሮንቶ አንድ እቃ ጫኝ መለስተኛ ተሽከርካሪ ባደረሰው አደጋ 10 አካል ጉዳተኞችን ሲገድል 15 ማቁሰሉ ተሰማ።

የካናዳ ፖሊስ አደጋው ሆን ተብሎ ነው የተፈጸመው ቢልም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን ማወቅ አልተቻለም ሲል ገልጿል።

የአደጋው ፈጻሚ የ25 አመቱ አሌክ ሚናሲያ አደጋውን ካደረሰ በኋላ ለመሸሽ ቢሞክርም ብዙም ሳይርቅ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል።

በካናዳ ቶሮንቶ ዮንጌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ሆን ተብሎ ተፈጸመ የተባለው አደጋ የተከሰተው።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ የ25 አመቱ አሌክ ሚናሲያ በእቃ ጫኝ መለስተኛ ተሽከርካሪ አካል ጉዳተኞች አሉበት በተባለው አካባቢ ባደረሰ አደጋ 10 ሰዎችን ገድሏል 15ቱን ደግሞ አቁስሏል።

በአካባቢው የነበሩት የአይን እማኞች ሁኔታው እጅግ ዘግናኝና ለመግለጽ እንኳን የሚከብድ ክስተት ነበር ብለውታል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ ድርጊቱ በምንም አይነት ቃል የማይገለጽና እጅግ አሳዛኝ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የካናዳ ፖሊስ አሌክ ሚናሲያ ድርጊቱን ሆን ብሎ ነው የፈጸመው ነገር ግን አላማው ምን እንደሆነ ግን አልታወቀም ብሏል።

አሌክ ሚናሲያ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ከአካባቢው ለመሰወር ሙከራ ማድረጉም ተሰምቷል።

ነገር ግን ብዙም አልተሳካላትም ሁለት ሕንጻዎችን ከተሻገረ በኋላ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎታል።

የሲቢሲ ዜና በድምጽ አስደግፎ ባሰራጨው ዘገባም ሚናሲያ በተያዘበት ወቅት ግደሉኝ እያለ መጮሁንና መሳሪያ ይዤያለሁ ብሎ ማስፈራራቱ ታውቋል።

የፖሊስ ሃይሉ ግን ማስፈራራቱን ወደ ጎን በማለት ሚናሲያን ያለምንም የተኩስ ልውውጥ በቁጥጥር ስር አውሎ በምርመራ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ትሩዲዮም ለነፍሳቸው ሳይሳሱ ወንጀለኛን ፊት ለፊት የተጋፈጡ ጀግኖች ሲሉ የፖሊስ ሃይሉን አመስግነዋል።