በከፋዞን ከ800 በላይ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ

በከፋዞን ከ800 በላይ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ
( ኢሳት ዜና መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ/ም ) በደቡብ ክልል በከፋ ዞን ይኖሩ የነበሩ ከ882 ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል። በ1946 ዓም ከሰላሌና ሜታሮ ቤት የተወሰዱ 20 ሺ የሚጠጉ የኦሮሞ ተወላጆች በከፋ ዞን እንዲሰፍሩ መደረጋቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ከ1983 ዓም ጀምሮ ቋንቋቸውን እንዳይጠቀሙ በመታገዳቸው ጥያቄ ማቅርባቸውን ተናግረዋል:፡ የአካባቢው ባለስልጣናት የመንጃ ጎሳዎችን በማስተባበር ጥያቄውን ባነሱት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማድረጋቸውን የገለጹት ነዋሪዎች፣ መስከረም 12 ቀን በተፈጸመው ጥቃት ውጊያ መጀመሩንና ዶማና ሴንተራ ቀበሌዎች የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸውን አስረድተዋል። በአሁኑ ሰዓት 882 የኦሮሞ ተወላጆች ዶማ ላይ ሰፍረው የሚገኙ ሲሆን፣ የከፋ ህዝብ እርዳታ እያደረገላቸው ቢሆንም፣ እርዳታ ለመስጠት የገቡ ሌሎችን ሰዎች የአካባቢው ባለስልጣናት አባረው መመለሳቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
መከላከያ ወደስ ፍራው ገብቶ እንዲያረጋጋ ተፈናቃዮች ጥያቄ በማቅረብ ላይ ናቸው። በጉዳዩዙሪያ የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።