በሶማሌ ክልል ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦች ተላልፈው እንዲሰጡ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 18/2011)በሶማሌ ክልል የጅምላ ግድያን ጨምሮ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦችን አሳልፈው እንዲሰጡ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ንግግር  መጀመሩ ተገለጸ።

በሶማሌ ክልል የሚገኘው አሰቃቂ እስር ቤት  ጄል ኦጋዴን  ሃላፊም ጎረቤት ሃገር ሶማሊያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የጄል ኦጋዴን ሃላፊ የነበሩት ግለሰብ በሶማሊያ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከጎረቤት ሶማሊያ   መንግስት ጋር  በተደረገ  ትብብር መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የህግ አማካሪ አቶ ጀማል ዲሪዬ ለኢሳት እንደገለጹት በቀድሞ የአብዲ ዒሌ አስተዳደር ዘመን በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመው በቱርክ፣ ኬኒ፣ ሶማሌያና ሌሎች ሃገራት የተደበቁ ወንጀለኞችን አድኖ የመያዙ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ሰሞኑንም ሀሰን ዲሬ በሚል መጠሪያቸው የሚታወቁት የጄል ኦጋዴን ሃላፊ ሀሰን ኢስማኤል ኢብራሂም ከሶማሊያ መንግስት ጋር በተደረገ ትብብር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ሃሰን ድሬ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ግድያና መጠነ ሰፊ የሰብዕዊ መብት ጥሰት በመፈጸም የሚፈለጉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጀማል በቅርቡ ለፍርድ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።

የፈጸሙት ወንጀል ከባድ በመሆኑ ጉዳያቸው በፌደራል መንግስት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በኩል ሊታይ እንደሚችልም አቶ ጀማል ዲሪዬ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ ገልጸዋል።