ሳዑዲ ለኢትዮጵያውያን የሰጠችውን ቪዛ ሰረዘች

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 18/2011)ሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገሯ ለስራ ለሚገቡ ኢትዮጵያውያን የሰጠችውን ቪዛ መሰረዟን አስታወቀች።

የሳዑዲ አረቢያ የስራና ሰራተኞች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ቪዛው የተሰረዘው ከኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በስራ ቅጥር ላይ ስምምነት ባለመደረሱ ነው።

ፋይል

ከረመዳን ጾም መግባት አስቀድሞ ሳዑዲ አረቢያ መድረስ ያለባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ስምምነት ባለመደረሱ ምክንያት መቅረታቸው ታውቋል።

ሳዑዲ አረቢያ በቅጥር ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ሰፊ ልዩነት መኖሩን ከመግለጽ ባሻገር ዝርዝር መረጃ አላቀረበችም።

ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያደርግነው ጥረት የሚመለከታቸው ሃላፊዎች የሉም የሚል ምላሽ በመሰጠቱ አልተሳካልንም።

የሳዑዲ አረቢያን የስራና የማህበራዊ ልማት ሚኒስቴርን ጠቅሶ ሳዑዲ ጋዜጣ እንደዘገበው ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን መቅጠሯን ለጊዜው አቁማለች።

በኢትዮጵያ በኩል ስምምነት ላይ መድረስ አልቻልንም የሚለው የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በዚህም ምክንያት ቪዛ ተሰጥቷቸው ወደ ሳዑዲ ሊገቡ በዝግጅት ላይ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን ቪዛቸው መሰረዙን አስታውቋል።

የረመዳን ጾም ከመግባቱ በፊት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ይገባሉ ተብለው በሳዑዲ ባለስልጣናት ፍቃድ ቪዛ የተሰጣቸው እነዚህ ኢትዮጵያውያን በሁለቱ ሃገራት መካከል ይደርሳል የተባለው ስምምነት ባለመሳካቱ በታቀደው ጊዜ ሳዑዲ አረቢያ መግባት እንዳልቻሉ ነው ዘገባው የሚያመለክተው።

ሳዑዲ አረቢያ በዝርዝር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተፈጠረውን ልዩነት አልገለጸችም።

ልዩነቱ ግን ጥልቅና ሰፊ መሆኑን የስራና ማህበራዊ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ባለፈው ከሁለት ሳምንት በፊት በሁለቱ ሀገራት የሚመለከታቸው ባለስልጣናት መካከል ውይይት መደረጉንና ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያውያኑን ቪዛ ከሰረዘች በኋላ ሀገሯ ገብተው መስራት ከፈቀደችላቸው 19 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያን ማስወጣቷን ሳዑዲ ጋዜጣ ዘግቧል።

ጋዜጣው በኢትዮጵያ በኩል ለዜጎቿ የጤንነት ምርመራ ማዕከል ለመመስረት ፍቃደኛ አይደለችም ሲል ስምምነቱ እንዳይደረስ ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ስምምነት ላለመደረሱ የኢትዮጵያን መንግስት ተጠያቂ ማድረጉም ተገልጿል።

ሳዑዲ አረቢያ ለስምምነቱ ያሳየችውን ቀናነት በኢትዮጵያ በኩል አልታየም ነው የሚሉት።

ጉዳዩን በተመለከተ ወደ ኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ደውለን በስም ያልተገለጹልን ሃላፊ ቀርበው ስለጉዳዩ የማውቀ ነገር የለም፣ የሚመለከተው አካል ለጊዜው በቢሮው የለም ሲሉ አጭር መልስ ሰጥተውናል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሚኒኬሽን ክፍል በተሰጠን ስልክ በመደወል ሃላፊውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን የስራ ዋስትናና ደህንነት በተመለከተ የቀደመው የስራ ኮንትራት አሰራር መቀየር እንዳለበት በማመን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የተለያዩ አዳዲስ ስምምነቶችን እያደረገ መሆኑን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በአሰሪዎቻቸው የሚደርስባቸውን በደልና የደሞዝ መከልከል ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በትኩረት የተነሳ ጉዳይ መሆኑም ተመልክቷል።

በሳዑዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ ለስራ የገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በትክክል ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።