ለፕሬዝዳንት ሙላቱ ህክምና የተጻፈው ደብዳቤ ሾልኮ ወጣ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 30/2010)

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለህክምና ወደ ቻይና ይሄዳሉ በሚል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የተጻፈላቸውን የውስጥ ደብዳቤና የተመደበላቸውን የሰው ሃይል ብዛት የሚያሳይ መረጃ ይፋ ሆነ።

የውስጥ ደብዳቤው ከፕሬዝዳንቱ ጋር ለህክምና ወደ ውጪ የሚጓዙት ሰዎች ብዛት 11 መሆኑን ያሳያል።

ለእያንዳንዳቸው ተጓዦችም የ10 ቀናት የውሎ አበል በውጭ ምንዛሪ እንደተዘጋጀላቸውና ለመጠባበቂያ የሚሆንም 10ሺ የአሜሪካን ዶላር እንደተመደበላቸው መረጃው አጋልጧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከደርግ ጋር ሲዋጉ መስዋዕትነትን ለከፈሉ 64 የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ሕወሃት ታጋዮች በማህበር ተደራጅተው ዘይትና ስኳር እንዲነግዱ ልዩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የትግራይ ክልል ንግድና ኢንደስትሪ ቢሮ ለንግድ ሚኒስቴር የጻፈው ደብዳቤ ሾልኮ ወጥቷል።

በስልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ የሚያጋልጡ ሚስጥራዊ ማስረጃዎች መውጣታቸው ቀጥሏል።

በቀድሞው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሃላፊ በአሁኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ በዶክተር ሃዱሽ ካሱ የፌስ ቡክ ገጽ እየተለቀቀ ያለው ሚስጥራዊ የመንግስት መረጃዎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።

እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በጥር 9/2010 ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጻፈው ደብዳቤ ትላንት ወጥቷል።

ይህ ደብዳቤ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ወደ ቻይና ለህክምና ለሚያደርጉት ጉዞ እሳቸውንና ባለቤታቸውን ጨምሮ ለ11 ሰዎች የጉዞ ፈቃድና የውሎ አበል ወጪ እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው።

በደብዳቤው ላይ የ11ቱ ግለሰቦች ስም ዝርዝር ተጠቅሶ ከቀን ውሎ አበል በተጨማሪ ለመጠባበቂያ 10ሺ የአሜሪካን ዶላር ወጪ ሆኖ እንዲከፈል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ትዕዛዝ መስጠቱ ተገልጿል።

ከ5 ወራት በፊት በተመሳሳይ የፕሬዝዳንቱ ባለቤት ወይዘሮ መአዛ አብርሃ ለህክምና ወደ ቻይና እንዲሄዱና አስፈላጊው ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሸፍን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ያዘዘበት ደብዳቤም ወጥቷል።

ወይዘሮ መአዛ አብርሃ ከቱርክ ወደ ኢትዮጵያ የተለያዩ እቃዎችን በማስገባት በከፍተኛ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብት እንደሆኑ ይነገራል።

ከዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር ወደ ቻይና የሚሄዱት 11 ሰዎች መሆናቸውን በተመለከተ ያነጋገርናቸው አንድ ዲፕሎማት አስገራሚ እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

የአሁኑ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጥቅማ ጥቅማቸው እንዳይከበርና ሕክምና እንዲከለከሉ በወቅቱ ውሳኔ ካሳለፉት ባለስልጣናት አንዱ ነበሩ።

ኦሕዴድ ሰሞኑን ባደረገው ስብሰባ ለዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ተሽከርካሪን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲከበሩላቸው መወሰኑ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ከትግራይ ክልል ንግድ ቢሮ ለንግድ ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ ከደርግ ጋር በነበረው ውጊያ መስዋዕትነትን ለከፈሉ 64 የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ሕወሃት ታጋዮች የተለየ ድጋፍ እንዲደረግ መጠየቁ ታውቋል።

ጥር 25/2010 በተጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደተመለከተው ገብረኪዳን በርሄና ሌሎች 64 አባላት ያሉበትን ማህበር ማቋቋማቸውን፣በወጣትነት እድሜያቸው ከደርግ ስርአት ጋር ሲፋለሙ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

ይሄ ማህበር ዘይትና ስኳር ለትግራይ ክልል እንዲያከፋፍል በተለየ መልኩ ድጋፍ እንዲደረግለት የሚጠይቅ ደብዳቤ ነው።

ላለፉት 27 አመታት ከደርግ ጋር የተደረገው ጦርነት እየተጠቀሰ የትግራይ ታጋዮች የተለየ ድጋፍ ሲደረግላቸው እንደቆየ የሚገልጹ አንዳንድ ወገኖች ይህ አይነቱ ድጋፍ መቼ ነው የሚቆመው ሲሉም ይጠይቃሉ።

ተቀናሽ የሕወሃት ሴት ታጋዮች ላቋቋሙት ማህበር የዘጠኙ ክልሎች የከተማ አስተዳደሮች ገንዘብ እንዲሰጡ ከፌደራል ታዘው በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ብር ድጋፍ እንዳደረጉ የሚታወስ ነው።