የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ፤የማልታ መንግስት ያሰራቸውን ከ50 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እንዲፈታ ጠየቀ

የንቅናቄው ዋና ስራ-አስፈፃሚ ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በማልታ ለተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ለሚስተር ማሪዮ ፍሪጀሪ በፃፉት ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያውኑ በእስር ላይ ረዘም ላለ ወራት መቆየታቸው  እጅግ እንዳሣሰባቸው ገልፀዋል።

እንዲሁም በእስር ቤት ውስጥ ሳሉ በተለይ ከጤናቸው ጋር በተያያዘ እያጋጠሙዋቸው ላሉ ችግሮች በቂ የህክምና አገልግሎትና መድሀኒት ሊያገኙ አለመቻላቸውም ድርጅታቸውን እጅግ እንደሚያሣስበው አቶ ኦባንግ ገልጸዋል።

አገራቸው ውስጥ በተፈጠረ ፖለቲካዊ ችግር ሳቢያ ወደ ሶስተኛ አገር የጥገኝነት ጥያቄ ለመጠየቅ ወደ ማልታ በመግባታቸው የተያዙት ከ50 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ከታሰሩ 9 ወራት ተቆጥረዋል።

ድርጅታቸው በታሰሩት ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄ  ጉዳይ ከስደተኞች ኮሚሽነሩ ጋር በመተባበር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ኦባንግ፤ ከእስር ተለቅቀው ጉዳያቸውን መከታተል በሚችሉበት ሁኔታ ከማልታ መንግስት ጋር ለመወያየትም የልኡካን ቡድን ወደ  ስፍራው ለመላክ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

 “ በተመድ ኮሚሽነር ተመዝግበው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ በነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ላይ የተፈፀመው ድርጊት ዓለማቀፍ ህግጋትን የጣሰ ነው”ያሉት አቶ ኦባንግ፤ የማልታ መንግስት ኢትዮጵያውያኑን በቶሎ እንዲፈታና ወደ ሶስተኛ አገር ለሚያደርጉት የጥገኝነት ጥያቄ በሩን ክፍት ሊያደርግላቸው ጠይቀዋል።

አቶ ኦባንግ ለተመድ ኮሚሽነር እንዳሉት፤  ኢትዮጵያውያኑ  ለማልታ ማህበረሰብ ችግር የሚፈጥሩ ወንጀለኞች አይደሉም። የኢትዮጵያውያኑ ጥፋት ያለ ህጋዊ ወረቀት የማልታን ድንበር ማቋረጣቸው ብቻ ነው። ይህን ደግሞ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግር የተጋረጠባቸው ማናቸውም ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ሢሰደዱ የሚያደርጉት ነው።

ይሁንና ከተጋፈጡት አስር በላይ የእስረኞቹ  ስጋት፤ በአንድ ፓርቲ፣ በአንድ ጠባብ የጎሳ ቡድንና በለየለት አምባገነን መዳፍ ውስጥ ወደገባቸው ኢትዮጵያ እንዳይመለሷቸው መሆኑን-ከአቶ ኦባንግ ደብደቤ ለመረዳት ተችሏል።