የተለያዩ ኩባንያ ዘበኞች ነጻ እርምጃ እንዲወስዱ ታዘዙ

ጥቅምት ፲፯ (አሥራ ሳባት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በተለያዩ የህወሃት/ኢህአዴግ እና የውጭ አገር ባለሃብቶች የገነቡዋቸውን ኩባንያዎች የሚጠብቁ ዘበኞች ከ12 ሰአታት በሁዋላ ወደ ኩባንያው በሚመጡ ሰዎች ወይም በኩባንያዎች ላይ አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ ብለው በጠረጠሩዋቸው ሰዎች ላይ ማንኛውንም እርምጃ እንዲወስዱ እንዲፈርሙ ተገደዋል። ይህንን እርምጃ መውሰድ ያልቻሉ ዘበኞች ለሚደርሰው ጉዳት ሃላፊነቱን ይወስዳሉ። ዘበኞቹ በማንኛውም ሰው ላይ የግድያ እርምጃ ቢወስዱ በአስቸኳይ አዋጁ መሰረት የህግ ተጠያቂነት አይኖርባቸውም። የእያካባቢው ፖሊሶችም በእነዚህ ዘበኞች ላይ ጥያቄ የማያቀርቡ ሲሆን፣ ማንኛውንም ነገር የሚከታተለው አዲስ የተቋቋመው ወታደራዊ እዙ ብቻ ይሆናል። ይህ የፖሊስን ስልጣን ከጥቅም ውጭ ያደረገ መመሪያ በፖሊሶችና በወታደራዊ እዙ መካከል አለመግባባት እየፈጠረ ነው።

በሌላ በኩል  ጥቅምት 13/2009 ዓ.ም ከአራዳ ጊዮርጊስ ከፍ ብሎ ማዕከላዊ አጠገብ በሚገኘው  በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መ/ቤት ከአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ለተውጣጡ የቀበሌ/ወረዳና  ዞን ፖሊስ አመራሮች የአስቸኳይ አዋጁን አፈጻጸም በሚመለከት መወሰድ ስላለበት እርምጃ  የአንድ ቀን የሥራ መመሪያ እንደተሰጣቸው ምንጮች ገልጸዋል።

ስብሰባው የተጠራው በፖሊስ መዋቅር ቢሆንም ጥሪውን ያስተላለፈው ወታደራዊ እዙ ወይም ኮማንድ ፖስቱ ነው። ሦስት የህወሃት ከፍተኛ የመከላከያ ሹማምንት “የአካባቢያችሁን ጸጥታ ለማስከበርና ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል በአስቸኳይ አዋጁ በተሰጣችሁ ሥልጣን መሰረት በማንኛውም የሁከት ተግባር በጠረጠራችሁት ላይና ኮሽታ በተሰማበት የቱንም እርምጃ መውሰድ ትችላላችሁ፡፡በሁከት ተጠርጣሪዎች የምትወስዱት እርምጃ ለሌሎች ሃሳቡ ላላቸው የጥፋት ኃይሎች ትምህርት የሚሰጥ ምንም ርህራሄ የማያስፈልገው የማያዳግም ጠንካራ እርምጃ መሆን አለበት፡፡ለዚህ አስፈላጊው የመንግስት ድጋፍ አይለያችሁም ፣ የኮማንድ ፖስቱ ለአፈጻጸሙ ከጎናችሁ ሆኖ ማናቸውንም የሎጂስቲክ አቅርቦትና አስፈላጊውን ሁሉ በየትኛውም ጊዜ ለማቅረብ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ስለሆነ ምንም ሥጋት ሊሰማችሁ አይገባም ›› ሲሉ የወረዳ አመራሮች ነጻ እርምጃ እንዲወስዱ አበረታተዋል።

አመራሮቹ ሲያብራሩም፣‹‹ ኮማንድ ፖስቱ ከመንግስት የተለየ መዋቅር እንደሚጠቀምና ለአሰራር በሚያመች መንገድ የኮማንድ ፖስት ቀጠናዎች መዋቀራቸውን በዚህም በሁለት አዋሳኝ ክልሎች ያሉ ቀበሌዎች፣ ወረዳዎችና ዞኖች በአንድ የኮማንድ ፖስት ቀጣና ውስጥ የተዋቀሩበት ሁኔታ መኖሩን እንድታውቁ ያስፈልጋል፤ ግዳጃችሁን የምትፈጽሙትም በዚህ የኮማንድ ፖስት ቀጠና ነው፤በመሆኑም ከምትሰሩበት ቀበሌና/ወረዳ ወይም ዞን ውጪም ለግዳጅ ልትሰማሩ ትችላላችሁ፣ ስለሆነም የምትሰሩበት የክልል መዋቅር ብዙም ሊያሳስባችሁ አይገባም… የቀጠናው አከፋፈል/አወቃቀር እና ዝርዝሩ በየቀጠናችሁ ይደርሳችኋል ›› ብለዋል።

በስብሰባው ላይ ከተገኙት የፖሊስ አመራሮች መካከል አንዳንዶች‹‹ በተጠረጠረ ሰው ላይ ያለምንም ርህራሄ  የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ማለት አስቸጋሪ ነው፣ ይህ አብረን ከኖርነውና ከምንኖረው ህዝብ ጋር ያጋጨናል፣ ከመንግስት ጋርም ህዝብን የበለጠ ያቃርናል፣ይህን  በምንሰራበት አካባቢ መፈጸም ከባድ ነው፣ ከሙያ ሥነ ምግባራችንም ሆነ ከአሰራር መርሃችን ይጋጫልና አፈጻጸሙ ላይ ችግር አያጋጥምም ?“ በማለት የጠየቁ ሲሆን “ ከአካባቢያችን/ ከክልላችን ውጪ ስንሰማራ የቋንቋ ችግርስ አያጋጥመንም ወይ? ለምሳሌ ከኦሮሚያ የመጣነው የሥራ ቋንቋውም ሆነ እኛ የምንችለው ኦሮምኛ ነው- ይህን እንዴት ታዩታላችሁ ?” የሚሉና ሌሎች ከአፈጻጸም ጋር የተገናኙ ችግሮችን የሚመለከቱ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡

የህወኃቶቹ መከላከያ ባለሥልጣናት በሰጡት ምላሽ ‹‹ ያለነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነው፤ ይህ የህግ፣ የመብትና ሰብዓዊነት  ጉዳይ አይደለም፣ የህልውና ጉዳይ ነው፣ ትግሉም የሞት የሽረት ነው፣ አሁን ጥያቄ የምናነሳበት ወቅት ሳይሆን የተግባር ሰዓት ነው፣ በመመሪያው መሰረት መፈጸም ብቻ ነው የሚጠበቅባችሁ፡፡ይህ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የራሳችሁም ህልውና ጉዳይ ነው፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ወደ ሥልጣን ቢመጡ ከማንም በላይ የምትጎዱት እናንተ ናችሁ፡፡ ለእነዚህ ኃይሎች ርህራሄ አያስፈልግም፣ የማያዳግም ቅጣት መቅጣት አለብን፣ እርምጃው የማያዳግምና እስከወዲያኛው አከርካሪያቸውን የሚሰብር መሆን አለበት፡፡ ›› በማለት ፖሊሶችን የሚያስጠነቅቅና የሚያስፈራራ መልስ ሰጥተዋል።

ፖሊሶቹ ከአዛዦች በተሰጠው መልስ ደስተኛ አልሆኑም።‹‹ከዚህ በኋላ የመንግስት መዋቅር አይሰራም፣ አስተዳደሩም በኮማንድ ፖስት ሥም በወታደራዊ ዕዝ ሥር ወድቋል ማለት ይቻላል፣ መከላከያ የአገሪቱን አመራር ተቆጣጥሮታል፣ መከላከያ ደግሞ በህወኃት አባላት ቁጥጥር ሥር ስለሆነ የመንግስት ሥልጣን በኢህአዴግ ሽፋን ከሚሰራበት በግልጽ ወደ ህወኃት እጅ ገብቷል ፣ ይህም በህዝቡ የተነሳውን ተቃውሞ እንዳያባብሰው ያሰጋል ››በማለት ምንጮች አስተያየታቸውን ገልጸዋል። በስብሰባው ላይ ከፌደራልም ሆነ ከአዲስ አበባና ኦሮሚያ ፖሊስ አመራሮች የተገኘ ሰው አልነበረም።

በሌላ በኩል በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋው አፈና በመጨመሩ ባለሃብቶች ሃብታቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ማሸሽ ጀምረዋል። በዚህም የተነሳ የዶላር ምንዛሬ እየጨመረ ነው። ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ ዶላር በጥቁር ገበያ ከ24ዩሮ ከ25 ሳንቲም ወደ 25 ዩሮ ከ50 ሳንቲም ማሸቀቡን፣ ዶላር ለማግኘት የሚታየው ወረፋ እንዲሁም ገንዘቡን ከባንክ የሚያወጣ ሰው አሃዝ መጨመሩን ምንጮች ገልጸዋል።

አብዛኛው ባለሃብት ስርዓቱ ይወድቃል የሚል እምነት እንዳለው የሚገልጹት ምንጮች፣ በዚህም የተነሳ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አመራጮችን ፈልጎ ድርጅቶችን ከማቋቋም እስካሁን ያጠራቀሙትን ገንዘብ ማሸሽ እየመረጡ ነው።

ቱሪዝምን ጨምሮ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የስራ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል።