ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የዲያስፖራ ቀን ለማክበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል

ሰኔ ፩ ( አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ወኪላችን ከሃረር እንደዘገበው የዲያስፖራውን ቀን ከሰኔ 24 እስከ ሃምሌ 24 የሚቆይ የዲያስፖራ ቀን በሃረር ለማክበር ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ዝግጅት እየተደረገ ነው። ወኪላችን እንደሚለው በአካባቢው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ባለበት እንዲሁም ድርቅ በገባበት ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አውጥቶ በአል ማክበር አሳዛኝ ነው።
የዲያስፖራ አባላትን በቤትና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች በመደለል ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የማግባባት ስራ እየተሰራ ነው። ገዢው ፓርቲ በእያመቱ የተለያዩ የዲያስፖራ ቀኖችን በማዘጋጀት ዲያስፖራው ፖለቲካዊ ድጋፍ እንዲሰጠው ከፍተኛ ሙከራ ቢያደርግም፣ እስካሁን ድረስ የሚጠብቀውን ያክል ፖለቲካዊ ድጋፍ አላገኘም።
ሰሞኑን በእስራኤል አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና ሚኒስትሮቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የተቃወሙበት እንዲሁም በሳውድ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውን ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል።
በአሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በሳውድአረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ ወረቀት የላችሁም በሚል ከአገር እንዲወጡ በተገደዱበት እና ኢትዮጵያውያን መንግስት በቂ ድጋፍ አላደረገልንም በማለት ከፍተኛ ተቀውሞ እያሰሙበት ባለበት ጊዜ ነው።