በሲዳማና በወላይታ ድንበሮች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ እየተሰራ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ

ሰኔ ፩ ( አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአመታት በፊት በወላይታና ሲዳማ ድንበሮች መካከል ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ ተነስቶ የነበረው ግጭት፣ የብዙ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈ በሁዋላ፣ ግችቱ በድጋሜ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ነዋሪዎች አስጠንቅቀዋል።
ከአመታት በፊት ተከስቶ በነበረው ግጭት 19 ሰዎች ሞተው፣ 65 ቤቶች ተቃጥለው የክልሉ መንግስት በጉዳዩ ገብቶ እንዳስቆመውና አወዛጋቢ የተባሉ ቦታዎች በወላይታ ዞን ክልል እንዲቆይ ተደርጎ ግጭቱ ቆሞ አካባቢው ተረጋግቶ እንደነበር፣ የወላይታ የዞን አስተዳዳሪና ይሄው ቦታ የሚገኝበት ወረዳ አስተዳዳሪ በጉዳዩ ላይ በወሰዱት አቋም ከሥልጣናቸው መባረራቸውን የሚያወሱት ነዋሪኦች፣ ግጭቱ በአቶ ሃይለማርያም አማካኝነት ደግም ሊቀሰቀስ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ የወላይታና ሲዳማ ዞን አዋሳኝ አራት አስተዳዳሪዎችን አስጠርተው በአራት ኪሎ መኖሪያቸው የምሳ ግብዣ እንዳደረጉላቸው፣ ከግብዣው በሁዋላ “አሁን በአስቸኳይ የፈለግኋችሁ ከዚህ በፊት በዚህ ድንበር አካባቢ የይገባኛል ጥያቄ ተነስቶ ግጭት መፈጠሩን ታስታውሳላችሁ፣ ይህ ችግር እስከዛሬም አልተፈታም፣ እየተንከባለለ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ተመሳሳይ ችግሮች በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ እያስከተሉ ያለውን ግጭትና አደጋ የምታውቁት ነው፤ በዚህ ረገድ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ አልወሰደም ተብሎ እየተወቀሰ ነው፡፡ ስለዚህ በእኛ አካባቢ ያለው ችግር በተመሳሳይ የዘገዬ ስለሆነ ወደዞናችሁና አዋሳኝ ወረዳ ሄዳችሁ ለህዝቡ ይህንኑ በማሳወቅ የግጭት መንስኤ የሆነው አካባቢ ወደ ሲዳማ ዞን እንዲካለል አድርጋችሁ የተደረሰበትን ስምምነት በአስቸኳይ እንድታሳውቁኝ ነው ›› በማለት ገልጸዋል፡፡
ተጋባዥ እንግዶች በሙሉ በሰሙት ነገር መደናገጣቸውን › ፣በተለይም ከወላይታ የመጣው አንደኛው ተወካይ ከፊቱ ላይ የማይደበቅ መደናገጥ ከማሳየት አልፎ ሲያጉረመርም የተመለከቱት አቶ ሃይለማርያም፣ ‹‹ ይህ የምንነጋገርበት ጉዳይ አይደለም፣ የራሳችን ፣ የድርጅታችንና የህዝባችን ህልውና፣ የአገራችን ልማትና ሠላም ጉዳይ ነው፤ በዚህ ጉዳይ ጥያቄ ማንሳትም ሆነ ቅሬታ ማሰማት አይቻልም፤ ተመልሳችሁ ሄዳችሁ ስምምነታችሁን በአጭር ጊዜ አሳውቁኝ ፡፡›› በማለት ማስጠንቀቂያ አዘል መመሪያ ሰጥተዋል።
ከወላይታ የመጡት ተጋባዥ እንግዶች ወደ ዞናቸው ተመልሰው ስለተነገራቸው ‹መመሪያ› ለሥራ ባልደረቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ሲያስረዱ በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ መደናገጥና መረበሽ ፈጥሯል፡፡
ይሄው መመሪያ ውስጥ-ለውስጥ ወደ ህዝቡ መድረሱን ያስረዱት ምንጮች፣ ህዝቡ “ይህ የኃይለማሪያም የበቀል በትር ነው” በማለት ውሳኔውን እያወገዙት ነው። ከዚህ በፊት አቶ ኃይለማሪያም ከተወለዱበት ወረዳ ህዝብ ጋር በገቡት ቅራኔ በምርጫ 2002 ከዚያ በፊት ኢህአዴግን ወክለው ከተወዳደሩት በጣም ዝቅተኛ ድምጽ በማግኘታቸው- ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ ለመታረቅ በሽማግሌ ቢጠይቁም፣ ህዝቡ “አልቀበልም” በማለቱ ‹‹ ተዋቸው፣ እኔን የመረጠኝ ድርጅቴ ኢህአዴግ እንጂ ህዝቡ አይደለም፣ አልወክለውም ›› ማለታቸውን ተከትሎ ፣ በምርጫ 2007 ከተወለዱበት ወረዳ ውጪ በሌላ ወረዳ መወዳደራቸውንና በዚህ ቅራኔ በወላይታ ህዝብ ላይ ቂም-መቋጠራቸውንና ጊዜ ጠብቀው ህዝቡን ለመጉዳት የሰነዘሩት የበቀል በትር ነው፡፡›› በማለት የአሁኑን ውሳኔ በቀጥታ ከአቶ ሃይለማርያም ጋር በመያያዝ ትችት እያቀረቡ ነው።
የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀበሌው ባሉ ሽማግሌዎች አማካኝነት ምክክር መጀመራቸውንና ውሳኔው ተግባራዊ አይሆንም በማለት በድፍረት በአደባባይ መናገር መጀመራቸው አካባቢውን አስፍሪ እያደረገው መጥቷል።
ከዚህ ባለፈም የአካባቢው ሽማግሌዎች ከዞኑ ውጪ ለሚኖሩ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ፣እንዲሁም በውጪ አገር ለሚገኙ የወላይታ ተወላጆች ይህን የበቀል በትር አብረው እንዲመክቱ፣ የሲዳማ ወንድም ህዝብም በዚህ ‹ሴራ› እንዳይጠለፍና ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈጽም፣ በማለት ጥሪ እያቀረቡ ነው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በአዲስአበባ የሚገኘው የ‹ወላይታ ልማት ማኅበር›› ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሥራ አቁሟል።
ስማቸው እንዳጠቀስ የፈለጉ ወኪላችን ያነጋገራቸው የወላይታ ተወላጆች “ጉዳዩ የወላይታና ሲዳማ ህዝብ ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ ለሁላችንም የተደገሰው ታላቅ የማጋጨትና ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ- ድግስ አካል ነውና አብረን ሆነን ካልመከትን በቀጣይ በሁሉም በየተራ የሚደርስ ነውና ‹‹ሳያቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ ተባብረን እሳቱን እናጥፋ/ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ በሲዳማ ህዝብ በኩል ውሳኔውን በተመለከተ ለማነጋገር ዘጋቢያችን ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኦሮሚያ እና ሱማሌ፣ በኦሮሚያ እና ጋምቤላ፣ በአማራ እና ትግራይ፣ በትግራይ እና አፋር ፣ ኦሮሚያ እና አዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ እና ሀረሪ፣ በኦሮሚያ እና ደቡብ (ጉጂ/ጌዲኦ) ድንበሮች መካከል ውዝግቦች ተነስተዋል። የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ፣ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ጉዳይ እንዲሁም በደቡብ ክልል የሰገን ዞን በአዲስ መልክ መዋቀርና የኮንሶ ህዝብ ጥያቄ እና ሌሎችም የመንነት ጥያቄዎች በቋንቋ ብቻ ላይ የተመሰረተው ‹ፈዴራሊዝም› በአገራችን ላይ ያጠመደው ‹የጊዜ ቦንብ › ለመፈንዳት እየተቃረበ መምጣቱን ያሳያል በማለት ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የተቃዋሚ ድርጅት መሪ ገልጸዋል። ሁኔታዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሱ፣ አገሪቱንም አደገኛ የሆነ የህልውና ፈተና እንደተጋረጠባት የጠቀሱት ፖለቲከኛው፣ ህዝቡ በህወሃት/ኢህአዴግ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግና ትኩረቱ ሁሉ የችግሩ ምንጭ በሆነው አመራሩ ላይ ሊሆን ይገባል” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።