ተመድ ለጋዜጠኞች ደህንነትና ጥበቃ ልዩ ተወካይ እንዲሾም አለም-አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጠየቁ

ኢሳት (የካቲት 17 ፥ 2009)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለጋዜጠኞች ደህንነትና ጥበቃ ልዩ ተወካይ እንዲሾም አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጠየቁ።

የኮሚቴ ቱ ፕሮጄትክ ጆርናሊስትስ CPJ  እና ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርድርስ (RSF) ተወካዮች ድርጅቱ ልዩ ተወካዮች በሚሾምበት ጉዳይ ዙሪያ ሃሙስ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ጋር መምከራቸውን የጋዜጠኛ መብት ተሟጋች ተቋማት ገልጸዋል።

የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ የቀረበላቸው ሃሳብ ለዴሞክራና የሰብዓዊ መብት መከበር ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ እርምጃን እንዲወስድ ቃል መግባታቸው ታውቋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት መንግስታት በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጽመው እስራትና ወከባ እንዲሁም ግድያ መባባሱን ምክንያት በማድረግ ሁለቱ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዩ በተባበሩት  መንግስታት ድርጅት ውስጥ ልዩ ተሰሚነት እንዲኖረው ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል።

በአለም ዙሪያ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን ወከባ እና እንግልት መሻሻል ባለማሳየቱ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል የሚወስደው ዕርምጃ አበረታች ነው ሲሉ የCPJ ሃላፊ ጀኦ’ል ሲሞን ተናግረዋል።

ድርጅቱ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የውሳኔ ሃሳቦችን ሲያስተላለፍ ቢቆይም ትርጉም ያለው ውጤት ሊገኝ አለመቻሉንና በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ወከባና እስራት ቀጥሎ እንደሚገኝ የጋዜጠኛ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ገልጸዋል።

ባለፈው የፈረንጆች 2016 አም ብቻ 78 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩትም በእስር ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

በጋዜጠኞች መብት ጥሰት የቆየ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱ ለጋዜጠኞች ምቹ ካልሆኑ የአለማችን ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን ሲፒጄ አስታውቋል።

በሃገሪቱ ከጥቂት አመታት በፊት ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የሽብርተኛ ወን ጀል ህግ ጋዜጠኞች ሙያዊ ግዴታቸውን በአግባቡ እንዳይወጡና ለእስር ምክንያት ሆኖ መቀጠሉን ድርጅቱ ገልጿል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ይኸው አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የኢትዮጵያ መንግስት ለእስር የዳረጋቸውን ጋዜጠኞች እንዲፈታ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ተወካይ እንዲሁም ከ100 በላይ አለም አቀፉ ድርጅቶች የድጋፍ ጥሪ ማድረጋቸውም ተመልክቷል።