14 ወጣት የሠራዊቱ አባላት የአቶ መለስን አገዛዝ በመቃወም የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን መቀላቀላቸው ተገለፀ።

ኢሳት ዜና :- የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ- በምህፃረ-ቃል “ትህዴን”  የወጣቶቹንና የወታደሮች ፎቶ አያይዞ ለኢሳት የላከው መግለጫ እንደሚያለክተው፤ የአቶ መለስን ሥርዓት ከድተው ወደ ትህዴን የተቀላቀሉት ወጣቶች፤ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ ፣ከትግራይና ከደቡብ ክልሎች  የመጡ ናቸው።

ወ/ር ብዙዓለም ሽፋራው እርቄ፣ አስር አለቃ ሁሴን መሃመድ አህመድ፣ ምክትል አስር አለቃ ቦጋለ ኩራቻ ፣ወታደር እድሪስ ሁሴን መሃመድ፣ አስር አለቃ ሁሴን ደመቀ ተገኘ፣ ምክትል አስር አለቃ ኢብራሂም ደግፌ ባንቲ ፣ወታደር ጸጉ ሃፍቶም መረሳ፣ አስር አለቃ ዋርሳው ባንቲ በሪሳ፣ ምክትል አስር አለቃ ታደመ ወይዳይ ጃጓድ፣ ወታደር አታኽልቲ ታረቀ ፍቃዱ፣ ፍስሃ ጸጋይ አውዓላ፣ ተወልደ መለስ መድሃንየ፣ አጸደ ማዓሾ ገ/ጻዲቕ፣ እና  ምሩፅ ዕቑባሚካኤል ገብሩ ናችው።

ወታደሮቹ  የነበሩበት እዝ ፣  ክ/ጦር ፣  ሬጅመንት ፣  ሻምበልና ፣  የመቶኛ ጓዳቸው  በድርጅቱ መግለጫ ላይ በዝርዝር ተመልክቷል።

ወጣቶቹ “ትህዴን”ን ለመቀላቀል የወሰኑት ፤በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት የህዝብን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የማያከብር በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

“ፀረ-ህዝቡ ስርዓት በብሄር ብሄረሰቦች ላይ እየፈጸመው ያለው በደልና ግፍ ከመቸውም ግዜ በላይ እየከፋ ነው”ያሉት ምክትል አስር አለቃ ሀሰን ደመቀና ምክትል አስር አለቃ ታደመ ወይዳይ፤በተለይ ባለፈው ወር በሀዲያ በተነሳው ግጭት ብዙ ሰዎች መገደላቸውና በርካታዎች ያለበደላቸው መታሰራቸው እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል።

“የሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች ሰራዊቱን በብሄር ፣ በማእረግና በጥቅማጥቅም በመለያየት የስልጣን እድሜያቸውን እያራዘሙ ናቸው”ያለው አስር አለቃ ሁሴን መሀመድ አህመድ ፤በተለይም ከ1997 ምርጫ በሁዋላ የተቀጠሩ አዲስ ምልምሎችን በማይጨበጥ ተስፋና በጥቅማጥቅም ለማታለል ጥረት ቢያደርጉም፤ አብዛኛው ሠራዊት በሥርዓቱ ላይ እምነት እንዳጣ  መረጃዎችን በመጥቀስ ተናግሯል።

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ትህዴን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በመምጣቱ ለገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ስጋት በሚሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል። መንግስት ስለከዱ ወታደሮች የሰጠው አስተያየት የለም።