በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ወደ አጎራባች ክልሎች መዛመቱ ስጋት እንደፈጠረ ተመድ አስታወቀ

ኢሳት (ህዳር 21 ፥ 2009)

በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋ ወደ አጎራባች ክልሎች በመዛመት ስጋት ማሳደሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረቡዕ አስታወቀ።

በሶማሌ፣ አፋር፣ ኦሮምያና ደቡብ ህዝቦች ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች ካለፈው ወር ጀምሮ በአካባቢው በተከሰተ አዲስ የድርቅ አደጋ ለሰብዓዊ እርዳታ መጋለጣቸው ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ይኸው አዲስ የድርቅ አደጋ በሰሜን ምስራቅ የአማራ ክልል እንዲሁም በአንዳንድ የደቡብ የትግራይ ዞኖች መታየቱን ድርጅቱ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርቱ አመልክቷል።

አዲስ የድርቅ አደጋ የተከሰተባቸው እነዚሁ አካባቢዎች ባለፈው አመት በተመሳሳይ ችግር ስር የቆዩ በመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ በስፍራው ያጋጠመው አደጋ የከፋ የሰብዓዊ ቀውስን ያስከትላል ተብሎ ተሰግቷል።

በአሁኑ ወቅት 9.7 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ አዲስ የተከሰተው የድርቅ አደጋ የተረጂዎች ቁጥር ከፍ እንዲል የሚያደርግ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።

በአካባቢው ለምግብ ድጋፍ የተጋለጡ ሰዎችን ቁጥር ለማወቅ የዳሰሳ ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን ያስታወቀው ድርጅቱ ክስተቱ ከሚገመተው በላይ አስጨናቂ መሆኑን አክሎ አመልክቷል።

ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች በሚገኙ ከ200 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የቤት እንስሶች መጨረሱ ይታወሳል።

አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ድርቁ የከፋ ችግር እንዳያስከትል ርብርብን ቢያደርጉም በሃገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ 9.7 ሚሊዮን ሰዎች እስከቀጣዩ የፈረንጆች አመት ድረስ የምግብ አርዳታን የሚሹ እንደሆነ ታውቋል።

በህንድ ውቂያኖስ ያጋጠመው ሙቀታማ የአየር ጸባይ በተለይ በኢትዮጵያ የከፋ የድርቅ አደጋ እንዲደርስ ማድረጉን የአለም የሜትሮሎጂ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ በ50 አመት ታሪክ ውስጥ ሲከሰት የከፋው እንደሆነም ተነግሯል።

ካለፈው አመት ጀምሮ ጉዳትን እያደረሰ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ በግብርና ምርት ተፅዕኖን በማሳደር በውጭ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆል እንዲመዘገብ ማድረጉን መረጃዎች የመለክታሉ።