ሁለት ኢትዮጵያውያንን የገደለው ግለሰብ ወደ ኢትዮጵያ ማምለጡ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 3/2010) አሜሪካ ውስጥ ሁለት ኢትዮጵያውያንን የገደለው ግለሰብ ወደ ኢትዮጵያ ማምለጡን ዋሽንግተን ፖስት ዘገበ።

ገዳዩን ኢትዮጵያ አሳልፋ አልሰጥም ማለቷና ግለሰቡ በነጻነት እየተንቀሳቀሰ መገኘቱም በዘገባው ተመልክቷል።

ሔኖክ ዮሀንስና ቅድስት ስሜነህ የተባሉትን ሁለት ወጣት ኢትዮጵያውያንን አምና በታህሳስ የገደለው ዮሀንስ ነሲቡ ግድያውን እንደፈጸመ ወደ ኢትዮጵያ ማምለጡም ታውቋል።

ሟቾቹ ሁለቱም በ22 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነበሩ።–ገዳይም በተመሳሳይ የዕድሜ ክልል የሚገኝ የ23 አመት ወጣት መሆኑም ታውቋል።

ገዳዩ በኢትዮጵያ በነጻነት እየተንቀሳቀሰ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን የወንጀል ድርጊቱን በኩራት እያስታወሰ በማህበራዊ መድረክ የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶችም የአሜሪካ ፖሊሶችን ትኩረት የሳቡ ሆነው ተገኝተዋል።

የሟች ቤተሰቦች በተለይም የቅድስት ስለሺ ስሜነህ አባት አቶ ስለሺ ስሜነህ ወንጀለኛውን በተመለከተ ዋሽንግተን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም ኤምባሲው ለዋሽንግተን ፖስት አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አስተያየት ከመስጠት መቆጠቡም በዘገባው ተመልክቷል።

በሁለተኛ ደረጃ ተማሪነቱ ወቅት ዌስት ስፕሪንግ ፊልድ ትምህርት ቤት እግር ኳስ ተጫዋች የነበረውን ሔኖክ ዮሀንስንና የኖርዝ ቨርጂኒያ ኮሌጅ ተማሪ የነበረችውን ቅድስት ስሜነህ የተገደሉት አምና እንደ አውሮፓውያኑ ታህሳስ 22/2015 እንደነበርም ማስታወስ ተችሏል።

ወጣቶቹ የተገደሉትም በዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ ቨርጂኒያ ግዛት ስፕሪንግ ፊልድ ውስጥ እንደሆነም ታውቋል።