(Aug. 27) የአቶ መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫዎችን እያወጡ ሲሆን፤ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ባወጣው መግለጫ ህዝብ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበት ሁሉን አቀፍ ጉባኤ እንዲጠራ ጠይቋል።
የሕወሀት/ኢህአዴግ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ አደረሳቸው ያላቸውን በደሎች የዘረዘረው መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ ከአጼ ሀይለስላሴ ጊዜ ጀምሮ የሚያነሳው የነጻነት ጥያቄ እንዳልተመለሰ ጠቅሶ፤ የህዝብ ብሶት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ፤ ብዙ ደም ስለፈሰሰና የአገር ኢኮኖሚ ስለተናጋ፤ ኢህአዴግ በሰለጠነ መንገድ ስልጣን ያለደም መፋሰስ ወደህዝብ እንዲያስተላልፍ ጥሪ አድርጓል።
ይህንንም የተሳካ ለማድረግ፤ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ፤ በሰላማዊም በትጥቅ ትግልም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ማህበራት፤ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች፤ ምሁራን፤ ሰራተኞች፤ አርሶ አደሮችና የገዢው ፓርቲ የሚገኙበት ብሄራዊ ጉባኤ እንዲዘጋጅ ጥሪ አድርገዋል።
በሌላ ዜና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (ዩዲጄ)፤ የአቶ መለስ ዜናዊን ሞት አስመለክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ኢህአዴግና በእሱ የሚመራው መንግስት በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ ህጋዊና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲያከናውን አሳስቧል።
አንድነት ባለፈው ረቡእ ባወጣው መግለጫ፤ “እንደተቃዋሚ ፓርቲም ሆነ እንደአገር ዜጋ ሁልግዜም የአገር ደህንነት፤ የህዝብ ሰላም፤ መረጋጋትና ብልጽግና እንደሚያሳስበው ገልጾ፤ ኢህአዴግ የአገርን ሉአላዊነትና ደህንነት፤ የህዝብን ሰላም ማረጋጋት እንዲሁም የማስጠበቅ ታሪካዊና አገራዊ ከፍተኛ ሃለፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል።”
በተያያዘ ዜና፤ ዘጠኝ በውጭ አገር የሚገኙና በትጥቅ ትግል የተሰማሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪል ማህበራት ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በገዢው ፓርቲ ላይ እምነት እንዲኖረው ከተፈለገ፤ ስርአቱ ማድረግ ይገባቸዋል የሚላቸውን ነጥቦች ዘርዝረዋል።
ከነዚህም ውስጥ ሽብርተኞችን ለመቆጣጠር በሚል የወጣው አዋጅ እንዲነሳ፤ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፤ የዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና፤ በልማት ስም ዜጎችን ከመሬታቸው ማፈናቀል እንዲቆም የሚሉት ይገኝባቸዋል።