(Aug. 27) የመንገስት መገናኛ ብዙሀን ስለ አቶ መለስ ጀግንነትና እንከን የለሽነት የሚያቀርቡት የግለሰብን ተክለ-ሰውነት ወይንም ፕረሰናሊቲ ከልት የመገንባት፤ እንዲሁም፤ በአቶ መለስና በፓርቲያቸው የተሰሩ ስህተቶችንና ደካማ ጎኖችን እንድንረሳ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው ሲሉ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ተናገሩ።
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ጽሁፍ አቶ መለስ ሰው እንደመሆናቸው፤ ድክመቶችና ስህተቶችም እያሉባቸው፤ እንደእንከን የለሽ ሰው የማቅረቡ ሂደት መጪው ትውልድ ከአቶ መለስ ህስተት እንዳይማር የሚያደረግና፤ በቀድሞ ነገስታት የሰለቸን የታሪክ አጻጻፍ ነው ብለዋል።
አቶ መለስ በርካታ ሕገመንግስቱን የሚጻረሩ ስራዎችን ሰርተዋል በማለት፤ የጸረ-ሽብር ህጉን፤ የመሬት ሊዝ አዋጁን፤ በ1997 ምርጫውን ተከትሎ የወጣውን ሕገወጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የፕሬስና የሲቪክ ማህበራት አዋጆችን የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ የኢትዮጵያዊያንን ሰብአዊ መብቶች በመጣስ የሚታወቁትን አቶ መለስ “እንደታላቅ መሪ” መሳል የሳቸውን ታሪክ የሚያበላሽና ሰው ከሳቸው የታሪክ ስህተት እንዳይማር የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በሌላ ዜና፤ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ም/ሊ፤ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላ ስለሳቸው የምንሰማው በሙሉ፤ “ለፓርቲው ይሁን ለአገሪቱ የመነጩት ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች” ከአቶ መለስ እንደሆነና፤ እርሳቸው ከሌሉ ፓርቲው የሚመራው እንደሚያጣ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጹ።
ከመገናኛ ብዙሀን የምንሰማው ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርግጥም ጠቅላይ እንደነበሩ ነው ያሉት አቶ ግርማ ሰይፉ፤ “ከአሁን በሁወላ አቶ መለስ የሚዳኙት በታሪክ ነው፤ ታሪክ ማንነታቸው ይመዝናል” ብለው፤ ኢህአዴግ የሰውየውን ታላቅነት ያለልክ ከማግዘፍ እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ኢህአዴግ 99.6 ከመቶ ባሸነፈበትና 547 ወንበሮች ባሉት ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውስጥ፤ ብቸኛው የተቃዋሚ ድርጅት ተመራጭ ሲሆኑ፤ ሁለተኛው ወንበር በቀድሞው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንትና የኢህአዴግ ደጋፊ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ መያዙ ይታወቃል።