ነሀሴ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኩማ አስተዳደር በተለምዶ ማዘጋጃ ቤት ተብሎ በሚጠራው ቅጥር ግቢ ውስጥ የጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት አስመልክቶ ሁለት ትልልቅ ድንኩዋኖችን በግቢው ውስጥ ተክሎአል።
አስተዳደሩ ከፌዴራል መንግስት በተለየ የከተማዋ ነዋሪዎች ሐዘናቸውን የሚገልጹበት ቦታ ያስፈልጋል በሚል ሁለት ትልልቅ ድንኩዋን ትላንት የተከለ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ሐዘናቸውን በለቅሶ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በይፋ ባይገለጽም የአቶ መለስ ሞት ከተሰማ በኃላ የአስተዳደሩ ልዩ ልዩ ቢሮዎች ምንም ዓይነት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችንም በቢሮአቸው ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖአል፡፡
አንድ አስተያየት ሰጪ በመንግስት ተቋም ደረጃ ድንኩዋነወ ተክሎ ሕዝብ እንዲያለቅስ ማነሳሳት ተራ የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ የሌለው ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው ሲል ተችቶታል፡፡አስተያየት ሰጪው አያይዞም ሕዝብ በራሱ መንገድ በየቤተ እምነቱ ሄዶ ሐዘኑን የሚገልጽበት ጸሎትም የሚያደርግበት ሥርዓት ቀድሞም ያለ መሆኑን በማስታወስ እስከ ቀብሩ ድረስ ከ15 ቀናት በላይ አገር ሐዘን ላይ እንዲቀመጥ ማድረግ ኃላፊነት ከሚሰማው አመራር የሚጠበቅ አይደለም ብሎአል፡፡
በተያያዘም የአዲስአበባ ዕድሮች ድንኩዋን በየመንደሩ በመትከልና ጥሩንባ እየነፉ ሕዝብ እንዲወጣ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ምንጮቻችን ጠቁሞ ሕዝብ በየመንደሩ ሐዘን ላይ እንዲቀመጥ የተፈለገበት ምክንያት ግን ግራ እንዳጋባው ተናግሮአል፡፡
አቶ በረከት ስምኦን በሒልተን ሆቴል በሰጡት አጭር መግለጫ “ሕዝቡ ለጠ/ሚኒስትር መለስ ሞት ባሳየው ሐዘን በኩል ግልጽ መልዕክት አስተላልፎልናል፡፡ያም መልዕክት አቶ መለስ የጀመረው የልማት መንገድ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡አዲሱ አመራር የሕዝቡን መልእክት በመቀበል የአቶ መለስን መስመር ተከትሎ ለመስራት ወስኗል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
አንዳንዶች የአቶ በረከት ንግግር ብስለት የጎደለው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡“ ማንኛውም ኢትዮጽያዊ እንኳንስ የሚያውቀውን የማያውቀውንም ሰው የሚቀብር፣የሚያስተዛዝን፣ቅን ሕዝብ ነው፡፡ይህ ሕዝብ አቶ መለስ የሰሩትንም ጥፋት በሆዱ ይዞ ሐዘኑን መግለጹን ብቻ በመውስድ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሯሯጥ ሕዝብን ካለማወቅ የመነጨ አጉል ስካር ነው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በትላንትና እለት በርካታ የምሽት ክለቦች በሀዘን ወቅት ድርጅታቸውን በመክፈትና መጠጦችንና በመሸጥ እንዲሁም ሙዚቃዎችን በመክፈታቸው ታሽገዋል። የክለቡ ባለቤቶችም በፖሊሶች ሲዋከቡ ውለዋል። በተለይ በሰሜን ሆቴል አካባቢ ዳትሰን በሚባለው ሰፈር ያሉ ምሽት ቤቶች በሙሉ ትናንት ምሽት ታሽገዋል።
ነጋዴዎች ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምስል የያዘ ቲሸርት ማሰሪያ ገንዘብ እንዲያዋጡ ተጠይቀዋል። ነጋዴዎች ለኢሳት እንደተናገሩት የሚችሉትን ያክል ገንዘብ እንዲሰጡ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
______________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide