የአቶ መለስ አስከሬን ዛሬ አዲስ አበባ ገባ

ነሀሴ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን በተገኙበት ዛሬ አስከሬናቸው አዲስ አበባ የገባው አቶ መለስ፣ በዋሽንት የሀዘን እንጉርጉሮ የታጀበ ወታደራዊ አቀባበል አቀባበል ተደርጎላቸዋል። አብዛኞቹ ባለስልጣናት በተለይም የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምኦንና የደህንነት አማካሪው አቶ ጸጋየ በርሄ  ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኖአቸው  አምርረው ሲያልቅሱ ታይተዋል።  ወይዘሮ አዜብ መስፍንና የአቶ መለስ ልጆችም እንዲሁ በእንባ ሲራጩ ታይተዋል።

ከቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ በቴዎድሮስ አደባባይ ቆይታ አድርጎ በፍል ውሀ በማለፍ ወደ ሚኒሊክ ቤተመንግስት ይገባል። ከዚያም ለ1 ሰአት ያክል በቤተመንግስት ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ሀዘናቸውን ይገልጻሉ ተብሎአል።

ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የአቶ መለስን ዜና እረፍት ህዝባዊ ለማድረግ ታዋቂ ሰዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ አትሌቶችን፣ አርቲስቶችን እና ሀብታሞችን በማነጋገር በኢቲቪና በራዲዮ ዝግጅት ለማቅረብ እየሰራ ነው።

አዲሱ ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚዎች በእርሳቸው ለመተዳዳር ቃል እንደገቡላቸው ተናገሩ

የ57አመቱን ጠቅላይ ሚኒሰትር ሞት ተከትሎ አዲሱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሀይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የአገሪቱን የአድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማስፈፀም ቃል ኪዳናቸውን አድሰዋል ብለዋል።

አቶ ሀይለማሪያም አቶ መለስ ለ30 ዓመታት እንደሻማ በመቅለጥ ታሪክ የሰሩ መሪ መሆናቸውን ገልጠው ከህመማቸው በማገገም ላይ በነበሩበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጋር በቅርበት እየተደዋወሉ በስራ ጉዳዮች ላይ ሲመክሩ እንደነበርም አትተዋል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide