ነሀሴ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢሳት ከሳምንታት በፊት ከዓለማቀፉ ግጭት ተንታኝ ቡድን ውስጥ ያሉ ምንጮቹን በመጥቀስ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ማረፋቸውን ይፋ ቢያደርግም፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩን አቶ በረከት ስምዖንን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትና በአገር ቤት የሚታተሙ አንዳንድ ጋዜጦች አቶ መለስ በቅርቡ ሥራ ለመጀመር በሚያስላቸው ጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሲገልፁ ቆይተዋል።
አቶ መለስ አርፈዋል፤አላረፉም የሚለው እሰጥ እገባ ባየለበት ሰዓት ሌላ አስደንጋጭ ዜና ተሰማ። አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ-ጳውሎስ በድንገት የማረፋቸው ዜና።
የፓትርያርኩ ዕረፍት በተገለጸ በ አራተኛው ቀን እነሆ ዛሬ ማለዳ የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ማረፋቸውን በይፋ አውጀ።
አቲቪ በዚሁ የዜና እወጃው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ አቶ መለስን ተክተው በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚቀጥሉም አስታውቋል።
እንደ ኢቲቪ ዘገባ፤ አቶ መለስ ያረፉት ትናንት ምሽት ነው።
ባደረባቸው ህመም ላለፉት ሁለት ወራት ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው በጤናቸው ላይ መሻሻል ከታየ በሁዋላ ከሁለት ቀን በፊት እንደገና በተፈጠረ ኢንፌክሽን ወደ ሆስፒታል ገብተው ክትትል ቢደረግላቸውም ትናንት ምሽት 5፡ ከ 40 ደቂቃ ላይ ማረፋቸውን ነው ኢቲቪ የገለፀው።
ይሁንና፤የፓትርያርኩን ማለፍ ተከትሎ እጅግ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እስከ ትናንት ምሽት ድረስ የተሰማቸውን የሀዘን መግለጫ ሲገልጹ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፦”ዕረፍት ላይ በጥሩ ሁኔታ ይገኛሉ”የተባሉትን የአቶ መለስ ዜናዊ የሀዘን መግለጫ በድምጽ እንኳ ሊያሰማ አለመቻሉ፤ በእርግጥ አቶ መለስ በህይወት ነበሩ ወይ? የሚል ጥያቄ የፈጠረባቸው ወገኖች፤አቶ መለስ ያረፉት ትናንት ነው መባሉን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።
በእርግጥ አልጀዚራ የአቶ መለስ አስከሬን ከብራሰልስ ሀኪም ቤት ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ ያሳየው ዛሬ ነው።
-ምንም ይህ አቶ መለስ የሞቱት ትናንት ምሽት ለመሆኑ ማረጋገጫ ሊሆን ባይችልም።
የህወሀቱ መስራች አቦይ ስብሀት ነጋ በቅርቡ ከ ኢሳት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ቃለ-ምልልስ ሲያደርጉ ጋዜጠኛ ሢሳይ አጌና፦” በ እርግጥ አቶ መለስ በህይወት አሉን?”፡ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብላቸው ፤ከት ብለው መሳቃቸው ይታወሳል።
አቶ መለስ ዜናዊ ማረፋቸው ዛሬ በመንገስት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ታዲያ በተለያዩ ዓለማቀፍ ሚዲያዎችና በማህበራዊ መገናኛዎች በርካታ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።
አልጀዚራ ፤ አቶ መለስ በኢኮኖሚ ዕድገት ረገድ ጥሩ ውጤት በማስመዝገባቸው የሚወደሱ ፤ በፀረ-ሽብር ህግ ሽፋን የተቃውሞ ድምፆችን በመጨፍለቃቸው ደግሞ የሚወገዙ መሪ መሆናቸውን ነው ያወሳው።
ቢቢሲ በበኩሉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ጥሩ ሥራ የሠሩት አቶ መለስ፤ በሰብዓዊ መብት አያያዝ በኩል ከፍ ያለ ወቀሳ እንደሚሰነዘርባቸው አመልክቷል።
የኬንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ የ አቶ መለስን ህልፈት ተከትሎ የሥልጣን ክፈተት እና ከፍተኛ አለመረጋጋት እንደሚፈጠር ሥጋታቸውን ለቢቢሲ ሲገልጹ፤ የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምዖን ግን ሁሉም ነገር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በነደፉት እቅድ መሰረት እንደሚቀጥልና አለመረጋጋት ሊፈጠር እንደማይችል ተናግረዋል።
እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው በድረ-ገጽ፣በፌስቡክ፣ በትዊተር እና በሌሎች ማህበራዊ መገናኛዎች በአቶ መለስ ሞት ዙሪያ አስተያታቸውን ሢሰጡ ውለዋል።
በአቶ መለስ ሞት ከፍ ያለ ሀዘን የተሰማቸው ወገኖች ኢትዮጵያ ወደ ታላቅ ሥፍራ የሚያሻግራትን ታላቅ ሰው እንዳጣች ሲገልጹ፤ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ኢትዮጵያን ላለፉት 21 ዓመታት በዋነኝነት ሲገድላት ከነበረ መሪ እንደተገላገለች ገልፀዋል።
መቅዲ ሀበሻ የተባለች ሴት በፌስ ቡክ አካውንቷ ላይ በለጠፈችው ጽሁፍ፦”ባገራችን ላይ የወደቀው ሀዘን ከምን ጊዜውም በላይ ከባድ ነውና ጌታ ሆይ መጽናናት እንድትሰጠን በተሰበረ ልብ እለምንሀለሁ” ብላለች።
ሀና መታሰቢያ የተባለች ደግሞ የህፃናት ልጆቻቸውን ፎቶ ይዘው በሚያለቅሱ እናት ምስል ግርጌ በለጠፈችው ጽሁፍ፦”በመለስ ሞት አዝኜ የማፈሰው አንድ ዘለላ እንባ የለኝም።እንባዬን በሙሉ መለስ በ1997 ሁለት ልጆቿን አስገድሎ ቷሪ ላሳጣት ምስኪን እናት አፍስሼ ጨርሸየዋለሁ”ብላለች።
አርቲስትና ገጣሚ ፋሲል ተካልኝ፦ ባሰፈረው ማስታወሻ ደግሞ ፦
፦“ትናንት ያስተዋልነው፤ዛሬ ጠፋ የለም
እግዚአብሔር ብቻ ነው-የሚኖር ዘላለም” ብሏል።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ባሰፈረው ጽሁፍ ደግሞ፤በተለያዩ ሚዲያዎች ስለ አቶ መለስ ሕመም፣ ከዚያም ዐልፎ ስለ መሞታቸው ቀደም ብሎ ሢሰማ መጨነቁን ጠቅሶ፤ “ ከሕመማቸው ተሽሏቸው ያለፉትን ሃያ ዓመታት ስሕተቶች ራሳቸው ያርሙታል፤ ያለፉትን ሃያ ዓመታት ጥንካሬዎችም በግለሰብ ላይ ሳይሆን በሥርዓት ላይ ይስኬዱታል ብዬ አምን ነበር፡፡ግን አልሆነም” ብሏል።
“ ኢትዮጵያ መሪዎቿ በሕይወት እያሉ ሥልጣን ሲቀያየሩ ሳታይ፣ የመሪዎች ለውጥ የሚመጣው አንድም በሞት አንድም በስደት ብቻ እንደሆነ ልንቀጥል ነው ማለት ነው” ያለው ዲያቆን ዳንኤል፤በአንድ ሰሞን ፓትርያርኩንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያጣንበት ምክንያት ምን ይሆን? የእግዚአብሔርስ መልእክቱ ምንድን ነው? ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ፦ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኀዘን ቦታ ላይ፦ ‹‹ሞት ታላቅ መጽሐፍ ነው፤ ነገርግን የሚያነበው የለም›› እንዳሉት፤ ከሰሞኑ ሁኔታ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ሌሎቻችንስ ምን እንማራለን? ሲል ጠይቋል።
ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተንታኞች የአቶ መለስ ማለፍ ለሰብዓዊ መብት፣ለፍትህ እና ለነፃነት የሚታገሉ ኢትዮጵያውያን የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወደ ድል በማምጣት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአንድ አገራዊ ሀሳብ ለማቆም ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ፤ ምዕራባውያንን ጨምሮ አንረዳንድ ወገኖች ደግሞ የሚፈጠረው የአመራር ክፍተት በኢትየጵያና በምስራቅ አፍሪቃ ቀንድ አለመረጋጋትን በመፍጠር የከፋ ሁኔታ እንዳያስከትል ሥጋታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።
ለዚህም ነው በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገር ያሉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይሎች ዓላማና ፕሮግራሞቻቸውን በማቻቻልና በአንድ ልብ በመሰባሰብ፤ የተሻለ አማራጭ ሀይል ሆነው እንዲወጡ እና መስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኘውን አገራቸውን ወደተሻለ ጎዳና እንዲመሩ ህዝባዊ ጥያቄው እየጎረፈ የሚገኘው።
____________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide