የአቶ መለስ ዜናዊን ዜና እረፍት ተከትሎ በመላው አገሪቱ ውጥረት ነግሷል

በአዲስ አበባ በርካታ ሰዎች ከእየ አካባቢያቸው ተሰባስበው የሚሆነውን በኢትዮጵያ ሬዲዮና እና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚከታተሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ህዝቡን የማረጋጋት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገድል በማወጅና እና በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ በማቅረብ ላይ ናቸው።

በመንግስታዊ ድርጅቶች እና ተቋማት ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ መውለብለብ ጀምሯል። የፌደራል ፖሊስ አባላት በየቦታው ፣ በሰፈሮች ውስጥ ሳይቀር ተበታትነው ይታያሉ።

በቀበሌዎችና ወረዳዎች ውስጥ የመደናገጥ ሁኔታ ይታያል፣ አግልግሎት በአግባቡ እየሰጡ አይደለም። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የግል ባንኮች ገንዘባቸውን በሚያወጡ ሰዎች ተጨናንቀዋል። ሁሉም ባንኮች ከውስጥና ከውጭ ጠባቂዎችን አጠናክረው ከፍተኛ ፍተሻ በማድረግ ስራቸውን ለመስራት እየሞከሩ ነው።

በትናንት ምሽት ላይ 1600 ብር የነበረው ነጭ ጤፍ በዛሬው እለት 200 ብር ጨምሮ 1800 ብር ገብቷል። ህዝቡ የሚመጣው አይታወቅም በማለት እየገዛ ነው።

በመላ አገሪቱ ከሀዘን ይልቅ የፍርሀት ድባብ እና ዝምታ ነግሷል።