ክቡር ገና የሚረገጥ ህዝብ ድንገት ይነሳል አሉ

“አንድ ህዝብ ዝም ብሎ ተኝቶ ሲረገጥ አይውልም፤ ድንገት ይነሳል፤ መተንፈሻ ያጣ ህዝብ ሌላ መንገድ በመፈለግ ለመተንፈስ ይሞክራል” ሲሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ክቡር ገና ተናገሩ።
አንድነት “በዴሞክራሲአዊ ስርአት ግንባታ የሲቪክ ማህበራት ሚና” በሚል ርእስ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተናጋሪ እንግዳ ሆነው የቀረቡት፤ ዶ/ር ክቡር ገና ከፍኖት ነጻነት አዘጋጆች ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፤ “ፖለቲካ ችግርን በውይይት መፍቻ መንገድ ሆኖ ሳለ” በኛ አገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ፤ በበጎ አይታይም ብለዋል።
ለዚህም፤ አንድነት ወዳዘጋጀው የውይይት መድረክ ለመሄድ ሲነሱ፤ እናታቸው እንዳይሄዱ እንደተማጸኗቸው እንደምሳሌ ጠቅሰዋል።
በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴ ላይ የተናገሩት ዶ/ር ክቡር ገና፤ መንግስት ሲቪክ ማህበራት እንዲያብቡ የማድረግ ከፍተኛ ሀላፊነት አለበት ብለዋል።
“መንግስት ከራሱ ውጪ ሌላ ሀሳብ ለማንሸራሸር ካልፈቀደ ችግር ይፈጠራል፤” ሲሉ የሙስሊሞቹን እንቅስቃሴ እንደምሳሌ አንስተዋል።
“የሙስሊሞቹ ጥያቄ መተንፈሻ አጣን የሚል ነው፤ ሁልግዜ አንድ ህዝብ ተኝቶ ሲረገጥ አይውልም፤ የሆነ ቦታ ላይ የራሱን መንገድ ይፈልጋል፤” እነዚህ ጥያቄዎች አንድ አይነት ነገር እንዲፈጥሩ ካልተደረገ ሌላ አይነት አካሄድ መፈጠሩ አይቀሬ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።