ዲፕሎማቶች እየኮበለሉ ነው ተባለ

(Aug. 17) ከአቶ መለስ ዜናዊ መሰወር ጋር ተያይዞ በውጭ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ወደአገር ቤት ቢጠሩም፤ ብዙዎቹ በነበሩበት አገር ወይንም ወደሌላ ሶስተኛ አገር በመኮብለል ጥገኝነት እየጠየቁ እንደሆነ የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
በህንድ የወ/ሮ ገነት ዘውዴ ምክትል ሆነው ሲሰሩ የነበሩት አቶ ደረጀ አስፋው ጄቶ ወደአሜሪካን እንደከዱና በአሜሪካን ጥገኝነት እንደጠየቁ ታማኝ ምንጮች ነግረውናል።
በሌላ ዜናም በካርቱም ዲፕሎማት ሆነው ሲሰሩ የቆዩትና ከዚህ ቀደም በጃፓንና በዱባይ ለረጂም ግዜ አምባሳደር በመሆን ያገለገሉት አቶ ተስፋዬ ደሳለኝም፤ ስራቸውን ለቀው ወደአሜሪካን እንደመጡ ለማወቅ ተችሏል።
ቀደም ሲል በቱርክ ዲፕሎማት የነበሩት አቶ ዮናስ መሀመድ ማይሎ እንዲሁ ወደአሜሪካን ተሰደው፤ በአሜሪካን ጥገኝነት እንዳገኙ ለማወቅ ተችሏል።
ብዙዎች የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በስራቸው ላይ ከመንግስት በሚደርስባቸው ፖለቲካዊ መድልዎና ጫና የተነሳ ስራቸውን እየለቀቁ ጥገኝነት እንደሚጠይቁ ሲናገሩ፤ በተለይ የአቶ መለስ መሰወርን ተከትሎ ወደኢትዮጵያ እንዲመለሱ ትእዛዝ ከተላለፈ በሁዋላ በውጭ አገራት ጥገኝነት የሚጠይቁ ኢትዮጵያዊያን ዲፕሎማቶች ቁጥር እንዳሻቀበ መረጃዎች ይተቁማሉ።
የጠ/ሚ/ር መለስን መሰወር ተከትሎ በሀገሪቱ የሰፈነው አለመረጋጋት የዲፕሎማቶችን ኩብለላ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን እያባባሰ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።