ሐምሌ ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ጋዜጠኛ ተመስገን በፌስ ቡክ ገጹ ባሰፈረው ማስታወሻ፦ በዛሬው ዕለት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተጠርቶ፦” ፍትህ ሚኒስቴር ክስ ስላቀረበብህ ቃልህን ስጥ”መባሉን ገልጿል።
ከቀናት በፊት የታገደቸው ጋዜጣ ትለቀቅና ለንባብ ትውላለች ብሎ ሢያስብ፣ እሱ እና ባልደረቦቹ ባልነበሩበትና ባልተከራከሩበት ችሎት ቀርባ ‹‹ትወረስ›› የሚል ወሳኔ እንደተላለፈባት ተመስገን አስታውሷል።
“ ካዛስ ምን ይሆናል?የተወረሰችውን ጋዜጣ መንግስት ሸጦ ገቢውን ይወስዳልን? ብለው ሲጠይቁ፦ ዳኛው‹‹አይ ለሽያጭ አትቀርብም፤ ትቃጠላለች እንጂ››የሚል መልስ በትናንትናው ዕለት እንደሰጧቸው፤አለያም እንደሱው አባባል እንዳረዷቸው ጠቁሟል።
“እነሆ ዛሬ ደግሞ ማዕከላዊ ምርመራ ጣቢያ በፌደራል ፖሊስ ተጠርቼ፦ ‹‹ፍትህ ሚንስቴር ክስ አቅርቦብሃልና ቃል ስጥ ተባልኩ”ያለው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ በሰባት የፍትህ ጋዜጣ እትሞች ስምንት ክስ እንደተመሰረተበት አመልክቷል።
ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል ለስምንቱም ክሶች መልስ ሢሰጥ መቆየቱን የጠቀሰው ተመስገን፤ የቀረቡበት ክሶች ሁሉ የዛሬ ዓመት በፍትህ ጋዜጣ ላይ የታታሙ ፅሁፎች መሆናቸውን ገልጿል፡፡
የኢሳት ወኪል ከስፍራው ያጠናቀረው መረጃ እንደሚያመለክተውም፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ዛሬ ከቀትር በሁዋላ ወደ ማዕከላዊ ተጠርቶ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 8፡00 ሰ ዓት እሰከ 10፡00 ሰዓት ተኩል ድረስ በወንጀል ምርመራ ቁጥር 75 ቢሮ ቆይቶ ወጥቷል።
ቃሉን ሰጥቶ ከማዕከላዊ የወጣው ተመስገን፦”ማዕከላዊ ከቀድሞ አሰራሩ ለውጥ አሳይቷል፡፡ ምክንያቱም እስከዛሬ ድረስ ተከስሼ ቃል ከሰጠሁ በኋላ በዋስ ነበር የምወጣው፤ በአሁኑ ክስ ግን ቃል ከሰጠሁ በኋላ ‹‹ምን አይነት ዋስ ላቅርብ?›› ብዬ ስጠይቅ፤- ‹‹ዝም ብለህ ሂድ፤ ዋስ አያስፈልግም፡፡ እዛው ፍርድ ቤት ከዐቃቤ ህግ ጋር ትገናኛላችሁ›› ተባልኩ፡፡ እኔም አመስግኜ ማዕከላዊ ድረስ ተከትለውኝ በመጡ አራት ባልደረቦቼ ታጅቤ ወጣሁ፡፡”ብሏል።
ይሁንና ጋዜጠኛ ተመስገን ከአቃቤ ህጉ ጋር የሚገናኙበት መቼ እና የትኛው ፍርድ ቤት እንደሆነ ያለው ነገር የለም።
ኢሳት ከትናንት በስቲያ ባስተላለፈው ዜና፦ “ተመስገን ደሳለኝ በሀገር መክዳት ወንጀል ሊከሰስ እንደሆነ ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል
ያስከሰሱት ፅሁፎችም፤-“ሞ ት የማይፈሩ ወጣቶች፣ አምባገነንነት ሲደመር ቅኝ ገዥ “ኢህአዴግ”በሚሉ ርዕሶች በራሱ በተመስገን የተፃፉ፤እንዲሁም “የብሔር ብሄረሰብ መብት እሰከ መጨፈር፣የሰሜን አፍሪቃ አብዮት እና ኢትዮጵያ፣ ከ ርዕዮታዊ መደናገር እስከ መንግስታዊ ሽፍትነት፣ የታክስ ጎራዴ፣ በ ኢትዮጵያ እንደ ሁለተኛ ቅኝ ተገዥነት” በሚሉ ርዕሶች በባልደረቦቹ እና በአምደኞች የተፃፉ ናቸው።
ሁሉም ጽሁፎች የዛሬ ዓመት በሐምሌ ወር እና ከዚያ በፊት በፍትህ ጋዜጣ ላይ የታተሙ ናቸው።
ከዓመት በፊት በታተሙ ጽሁፎች አሁን ክስ መመስረቱ አግራሞት እንደጫረበት ተመስገን ጠቁሟል።
ዘረሰናይ ምስጋናው እና አንተነህ ጌታቸው የተባሉ ዓቃቤ ህጎች ከበላይ አካል በመጣላቸው ትዕዛዝ መሰረት ክሱን እንዳዘጋጁ የማዕከላዊ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
ከዋና አዘጋጁ ከተመስገን ደሳለኝ ጋር ሌሎች የጋዜጣዋ አዘጋጆች፣ሪፖርተሮች፣ሥራ አስኪያጁ እና የጋዜጣው አከፋፋይም አብረው እንደሚከሰሱ ምንጮቹ ጠቁመዋል።የተጠቀሱት የተመስገን የሥራ ባልደረቦች በቅርቡ ወደ ማዕከላዊ ከተጠሩ በሁዋላ፤ “ሌላ ጊዜ ስንጠራችሁ ትመጣላችሁ” ተብለው ነው የተመለሱት::
ኢህአዴግ በተያዘው የክረምት ወር የፍትህ እና የፍኖተ ነፃነት ጋዜጠኞችን እና ከአንድነት ፓርቲ የተወሰኑ አመራሮችን ለማሰር ውሳኔ እንዳሳለፈ፤የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምንጮች ያደረሱንን መረጃ ዋቢ አድርገን መዘገባችን አይዘነጋም።
የኢህአዴግ መንግስት 2 ስዊድናውያንን ጨምሮ በአስራ አንድ ጋዜጠኞች ላይ የሽብርተኝነት ክስ መስርቶ በሁሉም ላይ ከ 8 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ የሚል ከባድ የእስር ውሳኔ አሳልፏል።
ውሳኔው ከተላለፈባቸው መካከል አምስቱ በእስር ቤት ሲሆኑ፤በሌሉበት ውሳኔ የተላለፈባቸው ስድስቱ ጋዜጠኞች በውጪ አገር ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide