አምነስቲ በሙስሊሞች ላይ አሰቃቂ ግፍ ተፈጽሟል አለ፡፡

ሐምሌ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህን ያስታወቀው “በሙስሊም ተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት ሳይፈጸም አልቀረም” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ላይ ነው።

ድርጅቱ እንዳለው በእስር ላይ የሚገኙት ሙስሊም ተቃዋሚዎች፣ አሰቃቂ ድብደባ ( ቶርቸር) እንደተፈጸመባቸው የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ ብሎአል።

አንዳንድ እስረኞች ከቤተሰቦቻቸው እንዳይገኙ ተደርጎ ለብቻቸው መታሰራቸውን፣ በአንዳንዶች ላይም ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ መፈጸሙን ገልጧል።

ፖሊስ ተቃውሞውን ለመበትን ሲል ከመጠን በላይ የሆነ ሀይል መጠቀሙን አምነስቲ ገልጧል።

ድምጻችን ይሰማ የኮሚቴ አባላትና ቢያንስ አንድ ጋዜጠኛም መታሰሩን የገለጠው ድርጅቱ፣ ሰዎቹ የታሰሩት ተፈጥሮአዊ የሆነውን ሀሳብን በነጻነት የመግልጽ መብታቸውን በመጠቀማቸው ነው ብሎአል።

አምነስቲ ከ100 እስከ 1000 የሚጠጉ ሙስሊሞች መታሰራቸውን ገልጦ፣ አንዲት ሴት በፖሊስ ልትደፈር እንደነበርም ጠቁሟል።

የኮሚቴው ሊቀመንበር አቡበክር አህመድ፣ ቃል አቀባዩ አህመዲን ጀበል፣ የኮሚቴው አባላት የሆኑት ካሚል ሸምሱ፣ ሱልጣን አማን፣ አደም ከሚል፣ ጀማል ያሲን እና መከተ ሙሄ በማእከላዊ እስርቤት ውስጥ ታስረው እንደሚገኙና አሰቃቂ የሆነ ድብደባ ሳይፈጸምባቸው እንዳልቀረ ድርጅቱ በሪፖርቱ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ማንኛውንም አይነት ተቃውሞ ለመታገስ ወኔ እየከዳው መምጣቱን፣ በፍትህ ጋዜጣ ላይ የተጣለውን እገዳ እና በሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ድብዳበ በአስረጅነት አቅርቧል።

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ተጠቅመው ተቃውሞ በማሰማታቸው የታሰሩትን ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲፈታ አምነስቲ ጠይቋል።

ኢሳት በትናንት ዘገባው በእስር ላይ በሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን  ላይ አሰቃቂ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው መዘገቡ ይታወሳል።

_____________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide