ሰኔ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ቤይሩት ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በር ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ስትደበደብ ከታየች ከቀናት በኋላ፤ ለሕክምና የገባችበት ሆስፒታል ውስጥ ሕይወቷን አጠፋች የተባለችው የአለም ደቻሳ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጸመ።
የ ዓለም የቀብር ሥነ-ስርዓት የተፈጸመው፤ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 27 ቀን በትውልድ ቦታዋ ቡ በግንደ-በረት ቤተሰቦቿን ጨምሮ የአካባቢው ማሕበረሰብ በተገኙበት ነው።
ለአራት ወራት ያህል እዚያው ቤይሩት የሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ በምርመራ ላይ የቆየው የዓለም ደቻሳ አስከሬን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ባለፈው ማክሰኞ ሲሆን፣ ቤተሰቦቿ ቦሌ አይሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አስከሬኑን እንደተቀበሉ ታውቋል።
“L.B.C.I” የተባለ የሊባኖስ ቴሌቪዥን የካቲት 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ባሰራጨው ፕሮግራም ፤ዓለም ደቻሳ ቤይሩት ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት አጠገብ ፤ወደ ሊባኖስ የወሰዳት ደላላ ወንድም በሆነ አሊማህፉዝ በተሰኘ ሰው ስትደበደብና ስትጎተት የሚያሳይ ፊልም ያስተላልፋል።
ይህ ቪድዮ በኢንተርኔት አማካኝነት በመላው ዓለም በመሰራጨቱ ፤ከየአቅጣጫው ቁጣ የተቀሰቀሰበት የሊባኖስ መንግስት፤ በጉዳዩ ላይ በቂ ምርመራ በማድረግ ጥፋተኛውን ለፍርድ እንደሚያቀርብ በወቅቱ ቢገልፅም፣ ባደባባይ ፤በዓለም አካል ላይ ጉዳት ሲያደርስባት የሚታየው ግለሰብም ሆነ አባሪው፤ እስካሁን ምንም አይነት እርምጃ ሳይወሰድባቸው በነፃነት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን ዓለም ለሕክምና እርዳታ “ካሪታስ” በተባለው የስደተኞች መርጃ ማዕከል አማካኝነት፤ “ዳኢር አል ሳሊብ “ የተሰኘ የስነ አዕምሮ ሆስፒታል ውስጥ ብትገባም፣ ከቀናት በኋላ ሕይወቷን በገዛ እጇ አጥፍታለች መባሉ አይዘነጋም።
ሆኖም ፤የተሟላ የሕክምና እርዳታ በሚሰጥበትና፣ ለሕሙማን ከፍተኛ ጥበቃና ክትትል በሚደረግበት የአዕምሮ በሽተኞች ሆስፒታል ውስጥ ዓለም እራሷን አጠፋች መባሉ፤ በብዙዎች ዘንድ ተዓማኒነት ያላገኘ ሰንካላ ምክኒያት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።
በመሆኑም፤የተለያዩ የኢትዮጵያውያን ሲቪክ ድርጅቶችን ጨምሮ፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ካሪታስ የስደተኞች መርጃ ማዕከል የሊባኖስ ቅርንጫፍ፣ የዴኒሽ ስደተኞች ምክር ቤት እና ሌሎችም ተቋማት፣ የሊባኖስ መንግስት የዓለም ደቻሳን አሟሟት በትክክል አጣርቶ የምርመራውን ውጤት ይፋ ያደርግ ዘንድ መጠየቃቸው አይዘነጋም።
እንደ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ፤ሰርታ ቤተሰቦቿን ለመርዳት ወደ ሊባኖስ ያቀናችው የ33 ዓመቷ ወጣት ዓለም ደቻሳ፤ ሁለት ሕፃናት ልጆቿንና አቅመ ደካማ ወላጆቿን የምትጦር ቅንና ታታሪ የነበረች ልጅ መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዓለም፤ የነበራት ጥቂት ገንዘብ ላይ ከሰው ተበድራ በመጨመር በደላላ አማካኝነት በታህሳስ ወር 2004 ዓ.ም ወደ ቤይሩት ብታቀናም፣ ለሁለት ወራት የሰራችባቸው ሁለት ቀጣሪዎቿ፤ ሌላው ቀርቶ የሰራችበትን ደመወዝ ሳይከፍሏት ለህልፈተ-ህይወት እንደዳረጓት ቅዱስሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ያጠናቀረው ዘገባ ያስረዳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide