ሰኔ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ፍትህ ጋዜጣንና ዋና አዘጋጁን ተመስገን ደሳለኝን -ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ለማስመሰል በአልሸባብ ስም ኢሜይል በመፃፍ የተደረገው የክፋትና የተንኮል ሙከራ ፤በራሱ በጋዜጠኛ ተመስገን መጋለጡ ይታወቃል።
“ሀገር በምን ይፈርሳል?” በሚል ርዕስ ተመስገን በዚህ ሳምንት ባሰፈረው ቀጣይ ጽሁፉ ፤የዚያ እኩይ ምግባር ፊታውራሪ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደሆነ ፦ የዘመንን ህትመቶች መጥቀሱን አውስቷል። ይህንን ተከትሎ በማግስቱ ቅዳሜ ማለትም፤ሰኔ 16/2004 ዓ.ም.በወጣው አዲስ ዘመን ላይ፤የጋዜጣው አዘጋጅ በተመስገን ላይ ቁጣና ማስፈራሪያ ሰንዝረዋል።
“አዘጋጁ ቁጣቸውን ሲገልፁ እንደ ከዚህ ቀደሙ በብዕር ስም ወይም በገደምዳሜ ለማድረግ እንኳ ጥቂት አልተጨነቁም። በግልፅ እና በድፍረት ነው ሀገር ጥዬ መጥፋት እንዳለብኝ የነገሩኝ”ብሏል ተመስገን። እንደ ጋዜጠኛ ተመስገን ገለፃ፤ ይህ ማስጠንቀቂያቸው የታተመው በገፅ 11፣ የፖለቲካ አምድ ላይ ሲሆን፤ አስፈራሪውም የገፁ ም/ዋና አዘጋጅ ሠይፈ ደርቤ ናቸው።
በምክትል አዘጋጁ በሰይፈ ስም፦ ‹‹ለሀገር ጥፋት ከመኖር…›› በሚል ያልተቋጨ ርእስ አዲስ ዘመን ባሰፈረው ጽሁፍ፡ – ‹‹ምንም እንኳን ፍትህ፤ ሽብር፣ ሽብር፣ አልሸባብ፣ አልሸባብ ብትልም፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የአንጋፋነት ስያሜ እየሰጠች ‹ይችን ሀገር ለቀን አንወጣም› የሚል ሀሳብ በየጊዜው ብታንፀባርቅም፤ ሀገር ከጠፋ በኋላ መቀመጫ እንደሌላት አለመጠርጠሩ ያስፈግጋል።… መሰደድና እንደገና የልማት ‹ሀሁ…› ውስጥ መግባት አንፈልግም። ከአዲስ መጀመርን አንሻም፤ በእምነት ሽፋን በየጊዜው የውዥንብር አጀንዳ በመቅረፅ ወሬ መፍጠር፣ የተፈጠረውን ወሬ ዜና ማድረግ፣ ሲሻ በእምነት ሽፋን፣ ካልሆነ በጦር ኃይል፣ አልሆን ሲል በመምህራን ጉዳይ፣ እንዲያ ሳይሆን በግንቦት ሰባት፣ እምቢ ሲል ‹… ጊዜ ለኩሉ› እያሉ መወትወት ብዕረኛም ጋዜጠኛም አያሰኝም። ሀገር መውደድና ለሀገር መኖር እንዲያ አይደለም። ይልቅ ለሀገር ጥፋት ከመኖር፤ ከሀገር መጥፋት ይሻላል።››ነው ያለው።
“ይህ አቋም፤ የመንግሥት ጋዜጣ አዘጋጅ አቋም ይሆናል ማለት ሊከብድ ቢችልም፤ አዘጋጁ በስማቸው አስከፃፉት ድረስ ፤ የእርሳቸው አድርጎ ከመቀበል ውጭ አማራጭ እንደሌለ የጠቀሰው ተመስገን፤ “ይህ ከሆነ ደግሞ የተለያዩ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፡ ፡ ለምሳሌ ለሀገር ጥፋት ከመኖር፤ ከሀገር መጥፋት ይሻላል ምን ማለት ነው? እና የምንጠፋውስ ወዴት ሀገር ነው? የሚሉትን ልናነሳ እንችላለን ብሏል።
ይህ ማስጠንቀቂያ ‹‹አልሸባብ ላከው›› ከተባለው ማስፈራሪያ የተለየ አይደለም የሚለው ተመስገን፤ “ ምን አልባት ልዩነት አለው ከተባለ እንኳ፤ የአዲስ ዘመኑ ‹‹ሀገር ለቆ መጥፋት›› የሚል አማራጭ ሲኖረው፤ የአልሸባቡ ግን ‹‹ህይወት እናጠፋለን›› የሚል አማራጭ ማስቀመጡ ብቻ ነው”ብሏል።
“የሆነ ሆኖ በፍትህ ላይም ሆነ በእኛ በአዘጋጆቹ ላይ ለሚደርስ አንዳች ‹‹ክፋት›› እኚህ የጋዜጣው አዘጋጅም ሆኑ ፤ማስጠንቀቂያውን ፦ በሚያዘጋጁት የፖለቲካ አምድ በኩል እንዲያደርሱ የላኳቸው ‹‹ሰዎች›› አስቀድመው ሀላፊነቱን ወስደዋል” ሲልም እየተጎነጎነ ያለውን ሴራ ከወዲሁ አጋልጧል።
“ መቼም ከዚህ የበለጠ መንግስታዊ የሽብር ድርጊት የትም ተሠምቶ እንደማያውቅ እርግጠኛ ነኝ”ያለው የፍትህ ዋና አዘጋጅ፤ “አልቃይዳ እና አልሸባብ እንኳ አደጋ ሲጥሉ እንዲህ ግልፅ ማስጠንቀቂያ ሠጥተው የሚያወቁ አይመስለኝም፡፡ እንግዲህ የሚሆነውን እናያለን”ብሏል።
ተመስገን፦“ሀገር በምን ይፈርሣል?” በሚል ጥያቄ አዘል ርዕስ ባስነበበው ጽሁፉ፤ጥያቄው ከባድ እንደሆነ በመጥቀስ፤ በ አሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ ለህዝባዊ አገልግሎት የተቋቋሙ መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሁሉ መስፈርታቸው ከ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ይልቅ ‹‹ኢህአዴጋዊነት›› የሚል ከሆነ ውሎ ማደሩን አመልክቷል።
“ ልክ ኢህአዴግ የሚባል ዳር ድንበሩ የተከበረ ሀገር ያለ ይመስል”ሲልም አክሏል።
ተመስገን አያይዞም፦“ግንባሩ፤በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ተራራና ወንዞቹ ሳይቀሩ ‹‹የግንቦት ሃያ ፍሬ ናቸው›› ወደ ማለት አዘንብሏል። ይህም ዕውን ይሆን ዘንድ ማደራጀት፣ ማደራጀት… አሁንም ማደራጀት። አባላትን ማብዛት፣ ማብዛት፣ ማብዛት… አሁንም ማብዛት የሚል ፍልስፍናን እንደዋነኛ አጀንዳ ይዟል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከኢህአዴግ ጥቅምም ሆነ ከፖሊሲው ጋር አንዳች ግንኙነት የሌለውን እና ለእስረኞች የሚሰጠውን ‹‹አመክሮ››፤” ያልተደራጀ እንደናፈቀው ይቀራል “የማለት አዝማሚያዎችን እየሰማን ነው” ብሏል።
ይህ አይነቱ ‹‹ጥርነፋ›› ደርግ ለመጨረሻ ጊዜ የተፍጨረጨረበትን፣ ነገር ግን ግብአተ መሬቱ ከመፈፀም ያልታደገውን ፦‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር›› መፈክርን ያስታውሰኛል”ሲልም ከ ኢህአዴግ ውጪ የሆኑ ዜጎች በዛች አገር ላይ ዕድል ፋንታ፤ጽዋ ተርታ እንደሌላቸው አመላክቷል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ‹‹መሬት መሬት አንድ›› ሲሉ በፃፉት ጽሁፍ ላይ፤ መሬቱ በሙሉ ለባለሀብት ተሸጦ ካለቀ፤ ቀሪው ኢትዮጵያዊ መሬቱ ቢወረር ለማን መሬት ብሎ አጥንትና ደሙን ይከሰክሳል? የሚል ይዘት ያለው ስጋታቸውን መግለፃቸውን ያስታወሰው ተመስገን፤” በእርግጥ ፕሮፍ ልክ ናቸው። የጋምቤላን መሬት የተቀራመቱት ህንድና ሳውዲአረቢያም ሆኑ፤ ዋና ዋና የከተሞቻችንን እምብርት እየገዛ ያለው መሀመድ አላሙዲ፤ ‹‹ሀገሪቱን በጥቂቶች የመጠቅለል›› ኢህአዴጋዊ ፍልስፍናን፤ ከዳር እያደረሱት ይመስለኛል”ብሏል።
“የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤትም ነው ሀገር የሚያፈርሰው። …ሀገር ህልውናዋ የሚረጋገጠው ዜጎች ‹‹ሀገሬ›› ሲሉ እንጂ የጥቂት ጉልበተኞች ‹‹ማረሻና ማጭድ›› ስትሆን አይደለም። አሁን እየሆነ ያለው ግን በግልባጩ ነው። ከዚህም በመነሳት ነው- ‹‹አይበለውና!›› እንደቀድሞዎቹ ቀውጢ ጊዜያት የሀገሪቱ ሉአላዊነት ቢደፈር፤ ማን ይሆን ‹‹ሀገሬን !ዳር ድንበሬን!›› ብሎ የሚሞተው? በሚል ስጋት የተዋጥነው፡፡ መቼም አላሙዲ እና የካራቺ ሩዝ አምራች ገበሬዎች፦ ‹‹ኢትዮጵያ የእኛ መመኪያ…›› እያሉ ሊዘምቱ እንደማይችሉ ግልፅ ነው”ብሏል-ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide