ሰኔ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የ11 ዓመታት እስራት ተፈርዶባቸው፣ አንድ ዓመት በእስር ቤት ያሳለፉት ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች “ይህ ዓመት በሕይወታችን እጅግ በጣም ረጅሙ ነው፣ እየደረሰብን ያለው ስነልቦናዊ ጉዳትም የማሰብ ችሎታችንን እያሳጣን ነው” ሲሉ አማረሩ።
ሁለቱ ጋዜጠኞች ባለፈው ሃሙስ እስር ቤቱ ድረስ ሊጠይቋቸው ለሄዱት የስዊድን ዲፕሎማቶች እንደገለፁት “እያሰብን ያለነው ስለምንበላው ምግብ፣ የምንተኛበት የሲሚንቶ ወለል እንዴት ሊሞቅ እንደሚችል፣ እና በበሽታ እንዳንጠቃ ነው።” ሲሉ መናገራቸውን ታይምስ ሊቭ የተሰኘው ድረ ገጽ ዘግቧል።
ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብየና ጋዜጠኛ ጆን ፔርሰን ለእስር የተዳረጉት አሸባሪዎችን በመርዳትና የሀገርን ሉአላዊነት በመድፈር ተወንጅለው ሲሆን፣ በሱማሊያ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመግባት፣ የኢሕአዴግ ስርዓት በአሸባሪነት የፈረጀውን የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር የተሰኘውን ድርጅትን እንቅስቃሴ በመዘገብ ላይ ሳሉ መያዛቸው ይታወሳል።
የስዊድን መንግስት፣ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሌሎችም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋዜጠኞቹ ላይ የተጣለውን እስር በመቃወም በተደጋጋሚ መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ በያዝነው የፈረንጆቹ አመት መጀመሪያ ላይም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ስዊድናውያን እንዲሁም የሌሎች አገር ተወላጆች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ሁለቱን ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ጨምሮ ያሰራቸውን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈታ መጠየቃቸውን፣ በወቅቱ በኢሳት መዘገባችን ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide