የነ አቶ መለስ ፕሮጀክት ከፍ ያለ ተቃውሞ ገጠመው

ሰኔ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለ ዘረፈ ብዙ እና በብዙ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኢንቭስትመንት ወጪ ተደርጎለት ኢትዮጵያን ፡ኬኒያን እና ደቡብ ሱዳንን ይጠቅማል ተብሎ ኬኒያ ውስጥ የግንባታ እቅድ የተያዘለት የላሙ ፕሮጅክት ፤ከማህበረሰብ እና ከአካባቤያዊ ተቆርቋሪዎች ከፍተኛ ነቀፌታ ገጠመው ፡፡

“ኒው አፍሪካ የተባለውን ወርሃዊ መጽሄት” ዋቤ በማድረግ ህብር ራዲዮ ከላስ ቬጋስ  እንደዘገበው ፤ይህ ከሃያ አራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ባላይ ውጪ የሚጠብቀው እና ከአንድ ሺህ ሄክታር  መሬት በላይ የሚያዳርሰው የወደብ፣የዓለማቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ፣የዘመናዊ አውራ ጎዳና፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ  ተከላ እና የቱሪስትቶች መናኸሪያ ግንባታ  ፕሮጀክት፤ ከኬኒያ አልፎ ሁለቱን የባህር በር አልባ  አገሮች ፤ ማለትም ኢትዮጵያን  እና ደቡብ ሱዳንን ጭምር ይጠቅማል ተበሎ በሦስቱ አገራት መሪዎች የመሰረት ድንጋዩ የተጣለው ከወራት በፊት ነው።

ይሁንና  በኬኒያ፣ በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መሪዎች ሰፊ ግምት እና ትኩረት የተሰጠው እና  ቻይናውያንን ጨምሮ የበርካታ አለማቀፍ ኢንስተሮችን  ቀልብ የሳበው ይህ ዘረፈ- ብዙ የላሙ ፕሮጀክት በአካባቢ ተንከባካቢዎች እና ተቆርቋሪዎች  ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ  እየተሰነዘረበት ነው።

ከ12 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ  የቆየችውና  የሰዋህሊኛ ቋንቋ እና የእስላማዊ ባህል መማሪያ  የሆነችው  ጥንታዊዋ የላሙ ከተማ፤ በአለማቀፉ የትምህርት ፡ የሳይንስ እና የባህል ማዕከል (ዮኔስኮ) ፤ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ካለፈው 2001 ዓ.ም  ጀምሮ በአለም የቅርስ ሃብትነት ተመዝግባለች።

እንደ አካባቢ ተቆርቋሪዎች ገለፃ፤ ከወራት በፊት በሶስቱ አገሮች የተጀመረው የላሙ ፕሮጀክት ፤ የአካባቢውን  ታሪካዊ ይዘት በመጉዳት   ከተማዋን ከዩኔስኮ የታሪክ ቅርስ መዝገብ ሊያስፍቃት ይችላል።

በኬኒያ የብሄራዊ ሙዚየም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ፋራህ አይደል በበኩላቸው፦ “ድህንነትን በማሰወገድ ረገድ የልማት እንቅስቃሴ መካሄዱን ብደግፍም፤ የላሙ ታሪካዊ ከተማን በመጠበቅ ረገድ  መንግስት ከአካባቢ ተቆርቃሪዎች ጋር ምንም አይነት ምክክር ሳያደርግ ወደ ፕሮጀክቱ መግባቱ በጣሙን እሳዝኖኛል”ብለዋል።

“ፕሮጀክቱን  የላሙን ታሪካዊ ገጽታ እንዳያበላሽ ጥንቃቄ  ይደረግ ዘንድ የሚያሳስብ አቤቱታችንን ለመንግስት አካላት ብናቀርብም እሰከአሁን ድረስ ምላሽ አላገኘንም’ያሉት  ዳይሬክተሩ፤ መንግስት በፕሮጀከቱ  በአሰቸካይ ጣልቃ በመግባት የላሙን ከተማ ታሪካዊ ገጽታ ይታደግ አንድ አሳስበዋል።

የጀርመኑ ድሬስደን ኤልበ ሸለቆ (Dresden Elbe Valley ) በዩኔስኮ ታሪካዊ ቅርስነት ከተመዘገብ በሁዋላ፤ በቅርቡ ሸለቆውን አቋርጦ የሚሄድና አራት መኪናዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ ድልድይ በመገንባቱ ሳቢያ  ከዩኔስኮ መዝገብ መፋቁን፤ ፋራህ አይደል በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ከወራት በፊት የላሙ ፕሮጅክት የመስረተ ድንጋይ ሲጣል በስፍራው የተገኙት የኬኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዴንጋ ለነዋሪው ህዝብ ባሰሙት ንግግር፦ ” ይህ፤ እኛ የምንገነባው ወደብ፤ ከዱባዩ ዓለማቀፍ ወደብ ያልተናነስ እጅግ ዘመናዊ በመሆኑ ፤ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ፦ ህይወታችሁ በብዙ ጎኑ ይሻሻላል ። እናንተ አሁን ይጎዳብናል የምትሉት  የላሙ አካባቢዊ ይዞታ፤ ወደፊት ከልማቱ ከምታገኙት ጠቀሜታ ጋር ሲነጻጸር፤ በውቅያኖስ ውስጥ እንደተወረወረች ትንሽ ጠጠር ያህል ነው የሚሆነው፡፡ስለዚህ ከበራፋችሁ እያንኳኳ ያለውን ዕድል እና አጋጣሚ በደስታ ተቀበሉት “ማለታቸው ይታወሳል።

አቶ መለስ ዜናዊ በበኩላቸው ፦” ግንባታው ሲጠናቀቅ በመሰረታዊ ልማት ወደ ሁዋላ የቀሩትን የ አካባቢውን  አገራት  ህዝቦች ያገናኛል ። በሰተመጨረሻም የምስራቅ እና የምእራብ አፍሪካን የባህር ዳርቻዎች በቀላሉ ለማገናኘት ያስችላል” ነበር ያሉት።

የላሙ ማህበረሰብ ግን “ኒው አፍሪካ” እንዳለው፦ አንደባለ ጉዳይ ስለ ፕሮጀክቱ ጉዳትም ሆነ ጥቅም ምንም አይነት መረጃ እንዳልተሰጣቸው እና ገለጻ እንዳልተደረገላቸው  ነው የአካባቢ ተቆርቋሪዎች  ሲናገሩ ሚደመጡት።

እንደውም  ከእለታዊ ህይወታቸው ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያለውን  ብቸኛ ሀብታቸውን፤ማለትም መሬታቸውን ከማጣት አልፈው ተገቢው የገንዘብ ካሳ ሳያገኙ ሜዳ ላይ  ሊወድቁ እንደሚችሉ የ አካባቢ ተሟጋቾቹ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ተቀማጭነቱ በጣሊያኑ የሮም ከተማ የሆነው አለማቀፉ የመሬት ባለቤትነት ተሟጋች ድርጅት፦”የናይሮቤ መንግስት በኢንቨስትመንት ስም ዜጎች የመሬት ባለቤትነት መበታቸውን የሚያረጋግጠውን ህገመንግስታዊ መብታቸውን እየሸረሸረው ይገኛል” በማለት  ነው  በፕሮጀክቱ ላይ ተቃውሞውን ያሰማው።

ፕሮጀክቱ በተያዘለት እቅድ እንኳ ቢካሄድ ደሀዎቹ የ አካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት በመጀመሪያው የግንባታ ደረጃ እንጂ ከተጠናቀቀ በሁዋላ  እንደማይሆን ምሳሌዎችን በመጥቀስ ያብራራው  ድርጅቱ፤አብዛኞቹ ነዋሪዎች የመሬት ባለቤት የሆኑት በባህላዊ ልምድ በመሆኑም፤ በተናጠልም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ተገቢውን ካሳ ሊያገኙ አይችሉም የሚለው ስጋት እያየለ መምጣቱንም ጠቁመዋል።

ከሁሉም በላይ ግን የላሙ ፕሮጀክት ሲጀመር  ጥናትና ምክክር አለመደረጉ፤ በአካባቢ ላ ይ የሚፈጥረው ጥፋትና ተጽዕኖ የከፋ እንደሚሆን ድርጅቱ ማስጠንቀቁን  የህብሩ ታምሩ ገዳ ያጠናቀረው ዘገባ ያመለክታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide