ሰኔ ፳፫ (ሃያ ሶስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ክርስቲያኑን እና ሙስሊሙን በማጋጨት ስልጣንን ማራዘም አይቻልም”፣ “ቀበሌ የካድሬ መፈልፈያ እንጂ የሙስሊም መሪዎች መምረጫ አይደለም”፣ “መንግስት በሃይማኖቶች ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ያቁም”፣ “በአሸባሪ ሽፋን ትግላችንን ማክሸፍ አይቻልም” የሚሉ መፈክሮችን የያዙ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በሚኒሶታ ሴንት ፖል ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደርገዋል።
ወደ 900 የሚጠጉ በርከት ያሉ የ እስልምና ተከታዮች ባደርጉት ተቃውሞ ሰልፍ ላይ ክርስቲያኖችም በመገኘት ድጋፋቸውን ሰጥተዋቸዋል።
“እስልምና የሰላም ሃይማኖት ነው” እያሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የዋሉት እነዚሁ ሰልፈኞች “እኛ ሙስሊም ነን፤ አሸባሪው መለስ ዜናዊ ነው” ብለዋል። በሴንት ፖል ስቴት ካፒቶል ደጃፍ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በሶማሊኛና በአረቢኛ መፈክሮች እና መልዕከቶች ቀርበዋል። የተለያዩ አባቶችም ንግግሮችን አድርገዋል።
“አማራውን ከትግሬ፣ ትግሬውን ከኦሮሞ ሁሉን ብሄሮች በማጋጨት ስልጣንን አራዝመዋል። አሁን ደግሞ በሃይማኖቶች ውስጥ ጣልቃ በመግባትና በማጋጨት ስልጣንን ለማራዘም መሞከር አይሰራም። እኛ አንድ ሕዝብ ነን። ሙስሊም የሰላም ሃይማኖት ነው” በማለት ንግግራቸውን በሰልፉ ላይ ያሰሙት አቶ የሱፍ ሥራቸውን እና ውድ ጊዜያቸውን ሰውተው በሰልፉ ላይ ለተገኙት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“በገደብ አሰሳ የጁምአ (የአርብ ጸሎት) አድርገው ሲወጡ በመንግስት ሃይሎች ጥይት የተቆሉት ወገኖቻችንን ጉዳይ የምንረሳው አይደለም፤ የነዚህ ወገኖቻችን ጉዳይም ተድበስብሶ የሚቀር መሆን የለበትም። አወሊያ ተነስቶ በመላው ኢትዮጵያ እየተቀጣጠለ ያለው የሙስሊሙ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያችን ይመለስ፣ መጅልስ ይውረድ፣ ቀበሌ የካድሬ መፈልፈያ እንጂ የመጅሊስ መምረጫ አይደለም የሚል ነው። እኛም በሚኒሶታ የምንኖር ኢትዮጵያውያን መንግስት የሙስሊሙን ጥያቄ እስኪመልስ፣ የእምነት ነጻነት እስከሚከበር አብረን እንጮሃለን።” ያሉት ደግሞ ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ናቸው።
ወደ 900 የሚጠጋው ሰልፈኛ ወንዶች በአንድ በኩል፣ ሴቶች በአንድ በኩል ቆመው ተቃውሟቸውን በሴንት ፖል ከተማ የነበረው ጠራራ ጸሐይ ሳይበግራቸው አሰምተዋል።
በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ለሙስሊም ወንድሞች እና እህቶች ድጋፍ ለመስጠት የክርስትና እምነት ተከታዮችም ተገኝተዋል ሲል የኢሳት የሚኒሶታ ወኪል የሆነው ሄኖክ አለማየሁ ዘግቧል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide