ጋዜጠኛ እስክንድር እና አቶ ናትናኤል ብርሀኑ ወደ ክፍላቸው ተመለሱ

ሰኔ ፳፫ (ሃያ ሶስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የጥፋተኝነት ብይን በተላለፈባቸው ማግስት ከታሰሩበት ክፍል  በሌሊት ተወስደው የነበሩት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና  አቶ ናትናኤል ብርሀኑ፤ ወደ ቀደመ የእስር ክፍላቸው ተመለሱ።

“ስህተቱ ስለታረመ እናመሰግናለን!” በሚል ርዕስ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ በፌስ ቡክ ባሰራጨው ዜና፤
ከትላንት በስቲያ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን  እና አቶ ናትናኤል ብርሃኑንን በውድቅት ሌሊት ከእስር ክፍላቸው አውጥተው የት እንደወሰዷቸው ባለመታወቁ ድንጋጤ ተፈጥሮ እንደነበር አውስቷል።

ሆኖም በትናንትናው ዕለት እስክንድርም ናትናኤልም ቀድሞ  ወደነበሩበት የ እስር ክፍል እንደተመለሱ እና ስንቅም እንደገባላቸው  ገልጿል።

እንደ ጋዜጠኛ ተመስገን ዘገባ፤እነ እስክንድር ተወስደው የነበሩት በተለምዶ የጠፉ እስረኞች  በሚታሰሩባትና  በጥበቃ ማማ ስር  ምትገኝ ሁለት ሜትር በሁለት  ሜትር ወደሆነች እና በድቅድቅ ጨላማ ወደተዋጠች ክፍል ውስጥ እንደነበር ታውቋል፡፡

የመሰወራቸው ነገር በፌስ ቡክ ከተገለፅ በኋላ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች፣ አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች እና አለም አቀፍ ሚዲያዎች ላሳዩት ፈጣን ምላሽ  ፈጣን ምላሽ ልባዊ ምስጋናውን የገለጸው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ “እንዲሁም ማረሚያቤቱ ፤ምክንያቱ ምንም ይህን ምን፤ ዘግይቶም ቢሆን ስህተቱን በማረሙ አመሰግናለሁ”ብሏል።

በቃሊቲ እስር ቤት የተወለደው የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ልጅ ናፍቆት እስክንድር  ከሁለት ቀናት በፊት የህመም ስሜት እየተሰማው “አባቴን ማዬት አለብኝ” በማለት  ከእናቱ ከጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል ጋር ወደ ቃሊቲ ቢሄዱም፤”በታሰረበት ክፍል  የለም፤ ወዴት እንደተወሰደ አናውቅም” የሚል የፖሊስ ምላሽ ተሰጥቷቸው ሳያዬት በሀዘን ተውጠው እንደተመለሱ መዘገቡ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide