ግንቦት7 የይስሙላውን ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳፋሪ ሲል አጣጣለው

ሰኔ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የግንቦት7 ንቅናቄ ባወጣው መግለጫ ” የመለስ ዜናዊ የይስሙላ ፍርድ ቤት በ24 ንጹሀን ዜጎች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ የሚገርም ” አይደለም ብሎአል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ አይነቱን የይስሙላና አንድን ወገን ለመጥቀም ተብሎ የተደረገውን የድፍረት አሳፋሪ ውሳኔ የለመደው ነው የሚለው ንቅናቄው፣ በጋዜጠኞች ላይ የተላለፈው ውሳኔም ሀሳብን የመግለጽን መብት ሙሉ በሙሉ የሚደመስስ ነው በማለት አለማቀፍ የመብት ተንከባካቢ ድርጅቶችን ዋቢ በማድረግ አውግዟል።
ግንቦት7 የኢትዮጵያ ህዝብ በሙስና የሻገተውን ፣ የፕሬስ ፣ የሰብአዊ መብት፣ የፍትህ እና የእኩልነት ጠላት የሆነውን የመለስ ዜናዊ መንግስት ፍጻሜ ለማወጅ በጋራ እንዲነሳም ጥሪ አቅርቧል። የመለስ ዜናዊ አምባገነን እና ዘረኛ አገዛዝ ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ እንዲነሳ ሲልም አክሏል።

አሜሪካና ሌሎች ምእራባዊያን አገሮች የመለስ ዜናዊን መረን የለቀቀ አካሄድ ማውገዝና የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱን ለማስከበር በሚያደርገው ጥረት ድጋፍ እንዲያደርጉ ንቅናቄው ጠይቋል።
በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው ሰሞኑን ጥፋተኛ የተባሉት ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ከግንቦት7 ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ይታወሳል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide