አቶ ጁኔይዲን ሳዶ የለውጥ ሠራዊት ግንባታ በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት እየተከናወነ አለመሆኑን ገለጡ

ሰኔ ፲፱ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሚኒስትሩ ዛሬ የመ/ቤታቸውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማው ባቀረቡበት መድረክ ላይ ከም/ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሸ በአመለካከት እና በክህሎት ችግሮች ምክንያት ዕቅዱ በሚፈለገው ደረጃ እየተፈጸመ አለመሆኑን አምነዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ግልጽና ተጠያቂነት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በየደረጃው የሰፈነበት ሲቪል ሰርቪስ ለመፍጠር በየተቋማቱ የለውጥ ሠራዊት መገንባት እንደመሳሪያ በመውሰድ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ በእስካሁኑም

እንቅስቃሴ በየመድረኩ የተፈጠሩ ብዥታዎችን ለማጥራት መሞከሩን ጠቅሰዋል፡፡

የለውጥ ሠራዊት ግንባታው በሶስት ክፍሎች ማለትም የሕዝብ ክንፍ፣የመንግስት ክንፍ፣ግንባር ቀደም በሚል መከፈሉን ያስታወሱት አቶ ጁኔይዲን ግንባር ቀደም ማንነው፣እንዴትስ ይለያል የሚሉ ብዥታዎችን ለማጥራት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

እንደሳቸው ገለጻ ከሆነ “ግንባር ቀደም” የሚባለው ማንኛውንም ምርጥ የሥራ አፈጻጸም ያሳየ ሰራተኛ ነው፡፡ይህ ሠራተኛ በቡድን መሪነት፣በሥራ ሒደት መሪነት በተለያዩ ኮሚቴዎች አመራር ላይ ሊመደብ የሚችል ነው፡፡“የሕዝብ ክንፍ” የሚባለው በአገልግሎት አሰጣጥ የሚታዩ ችግሮችን የሚገልጹ አካላትን ነው፡፡“የመንግሥት ክንፍ” የበላይ አመራሩ፣ መካከለኛውና ሠራተኛው ተቀናጅተው የሚሰሩበት አግባብ ነው ተብሏል፡፡

በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ሠራተኛው በየሳምንቱ የግምገማ ሥርዓት ዘርግቶ እየሰራበት መሆኑ፣ይህ ሒደትም የመማማር ባህል እንዲጎለብት፣የቡድን ሰሜት እንዲፈጠር ችግሮች ቶሎ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በክልሎች የለውጥ ሠራዊት ግንባታ ከጋምቤላ ክልል በስተቀር መጀመሩን ጠቁመው አፈጻጸሙ ግን በተቀመጠው ደረጃና አቅጣጫ መሰረት እየተጓዘ አይደለም ብለዋል፡፡

አቶ ጁነዲን ይህን ቢሉም በተግባር እየተደረገ ያለው ግን ሰራተኛውን አንድ ለአምስት በማደራጀት ለኢህአዴግ ያለውን ታማኝነት መግለጥ ነው። የመንግስት ሰራተኛው የኢህአዴግን አደረጃጃት በመቃወም፣ በሲቪል ሰርቪሱ ላይ እያመጸ እንደሚገኝ ነው ዘጋቢያችን የገለጠው። ከዚህ ቀደም በመቶ ሚሊዮኖች ብር ወጥቶባቸው ተግባራዊ እንዲሆኑ የተደረጉት የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ማሻሻያ፣ አቅም ግንባታ፣ ቢፒር፣ ቢሲሲ፣ የተባሉት አደረጃጃቶች ሁሉ ውጤት አልባ የሆኑት ሰራተኛው ለኢህአዴግ መንግስት ያለው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ ነው። ሪፖርተርን ጨምሮ በርካታ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ሲቪል ሰርቪሱ በኢህአዴግ ላይ የዝምታ ተቃውሞ እያካሄደ ነው በማለት መውቀስ ጀምረዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide